እጅግ ባማረ መልኩ ሁለንተናዊ ዕድሳት የተካሄደለት የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ!!
በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ባማረ መልኩ ሁለንተናዊ ዕድሳት የተካሄደለት የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ።
ከአንድ ዓመት በፊት ማለትም መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባታዊ መልካም ፈቃድ ፅላቱን ጊዜያዊ መቃኞ በማስገባት ዕድሳቱ እንዲጀምር መደረጉ የሚታወስ ነው።
በ2013 ዓ.ም ወርኃ ሚያዚያ የተጀመረው ሁለንተናዊ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ዕድሳት እጅግ ባማረ መልኩ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በትናንትናው ዕለት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ ፅላቱ ወደ መንበረ ክብሩ ተመልሷል።
አባቶች ሌሊቱን በማሕሌት እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ያደሩ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውም በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እየተመራ ተካሂዷል።
በብፁዕነታቸው መልካም ፈቃድ መ/ር ዘላለም ወንድሙ አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት “መጻጒዕ” አስመልክተው ትምህርት ሰጥተዋል።
“መጻጒዕ” ማለት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዘ በሽተኛ ማለት መሆኑን ጠቅሰው ስያሜውም ከቅዱስ ያሬድ እንደተገኘ አውስተዋል።
የዕለቱ ሙሉ ታሪክ የሚገኝበትን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5፥ ከቁጥር 1 እስከ 25 ያለውን ክፍል አንስተው አብራርተዋል።
አያይዘውም በአሁን ሰዓት ዘረኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣መከፋፈል፣ መዋሸት፣ መስረቅና መጨካከን ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየተባባሱ የመጡ አስከፊ በሽታዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ራሱን ከእነዚህ አስከፊ በሽታዎች እንዲጠብቅ መልእክት አስተላልፈዋል።
ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የሚፈውስ እርሱ መድኃኔዓለም መሆኑን ገልጸው ሁላችንም ዘወትር በእምነትና በንስሐ ወደ እርሱ መቅረብ እንደሚገባን አስተምረዋል።
ከደብሩ አስተዳዳሪ ክቡር መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ ጀምሮ ዕድሳቱ እንዲካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት በሙሉ ልዩ ልዩ የሽልማት ስጦታና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።
በተለይ የደብሩ አስተዳዳሪ በአንድ ዓመት ውስጥ በፍጥነትና እጅግ በሚገርም ሁኔታ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ እንዲታደስ የሰጡትን ድንቅ አመራር አስመልክቶ የደብሩ ምክትል ሊቀመንበር ምስክር ሰጥተዋል።
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምእመናንን በማስተባበር ክቡር አስተዳዳሪው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ባለ ሁለት መኝታ ኮንደሚኒየም ቤት ገዝቶ በሽልማት እንደሚያበረክትላቸው ቃል ገብቷል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ ባደረጉት ንግግር መጋቢት 11 ቀን 1952 ዓ.ም የመጀመሪያው ቅዳሴ ቤት የተከበረበት ዕለት መሆኑን አውስተው ከ62 ዓመታት በኋላ ታሪክ ራሱን መድገሙን ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕድሳቱ አልቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ለሕዝበ ምእመኑም እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ከአንድ ዓመት በፊት የነበረውን ሕንጻ ቤተክርስቲያንና አሁን በሚገርም ሁኔታ የታደሰውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን አነጻጽረው ተናግረዋል።
ሰው የተፈጠረበት አንዱ ዓላማ እግዚአብሔርን ለማመስገን መሆኑን አውስተው ሁላችንም ከቅዱስ ያሬድ ምስጋናን ልንማር ያስፈልጋል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ዕድሳቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ለተባበሩትና ለተራዱት አካላት በመሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው ሰበካ ጉባኤው ደብሩ በካቴድራል ማዕረግ እንዲጠራ የጠየቀውን ጥያቄ ከብፁዓን አባቶች ጋር ተማክረው እንደሚወስኑ ገልጸዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ፣ የአድባራትና ገደማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርከታ ምእመናን ተገኝተዋል።
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ(ፎቶ)