” መጻጒዕ “
አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት “መጻጒዕ”
ይባላል። ትርጉሙም በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዘ በሽተኛ ማለት ሲሆን ስያሜውን ያገኘው ከቅዱስ ያሬድ ቢሆንም የዕለቱ ሙሉ ታሪክ የሚገኘው ግን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩-፳፭ ባለው ክፍል ላይ ነው።
በዚህ ዕለት የእግዚአብሔር አምላካችን ፈዋሽነትና አዳኝነት እንዲሁም ታዳጊነትና የወደቁትን የማይረሳ እውነተኛ መድኃኒት መሆኑ የሚዘከርበትና ምሥጋና የሚቀርብበት ነው።
ዘማሪው ቅዱስ ዳዊትም “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፣ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፣ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ” እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፣ መኝታውንም ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፣ እኔም አቤቱ ማረኝ እልሃለሁ በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት በዝማሬው
አረጋግጧል።
ከላይ በተጠቀሰው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል በሀገረ ኢየሩሳሌም ከበጎች በር አጠገብ የሚገኝ ቤተሳይዳ (ቤተዛታም) በሚል መጠሪያ የሚታወቅና አምስት መመላለሻዎች ያሉት መጠመቂያ እንደነበር ተገልጿል።
በዚያም ሥፍራ ልዩ ልዩ ደዌና ችግር ያለባቸው በሽተኞች፣ ዕውሮች፣አንካሶች፣ ሰውነታቸው የሰለለ ሁሉ ፈውስ አጥተው ፈውስ ፈልገው በአከባቢው ዳስ ጥለው ደጅ የሚጠኑበት ቦታ ነው።
ነገር ግን የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሀውን አናውጦ ከወጣ በኋላ ቀድሞ የገባ አንድ ሰው ብቻ የሚፈውስበት የምሕረት ቦታ ነው።
በተለያየ ዓይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል ደዌው የጸናበት፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ፣በአልጋ ቍራኛ ተይዞ የኖረ፤ ከደዌው ጽናት የተነሣ “መጻጒዕ” ተብሎ የተጠራና ተስፈ የቆረጠ በሽተኛ በዚያ ነበር፡፡ መጻጒዕ ማለት ስም አይደለም፣ ደዌ የጸናበት በሽተኛ ሕመምተኛ ማለት ነው እንጂ፣ሰውየው ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ ጠፍቶ በበሽታው ሲጠራ የነበረ ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ በሽተኞችን ሲጎበኝ ተስፋ መቁረጡን ተመልክቶ “አልጋህን ተሸክመህ ሒድ” ብሎ 38 ዘመን የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረጉ የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ሳምንቱ “መጻጒዕ” ተብሎ ተሰይሟል፡፡
ዛሬም ቢኾን በእኛ በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ፤ የሥጋውን ደዌ ሐኪሞች ያውቁታል፣ይፈውሱታልም ከዚህ የከፉ ደዌያት ግን የነፍስ ናቸው።
በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፤ ሰውነታቸው የሰለለ፤ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፤ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን አሁንም አሉ፣ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡
በጥቅሉ የመጻጉዕ ሳምንትን ስናስብ በልዩ ልዩ ችግር የተነሣ ተስፋ የቆረጠችን ነፍስ እግዚአብሔር እንደ ሚጎበኝ የሚያስረዳ ሲሆን ነገር ግን የተሰበረው ልባችን እንዲጠገን: የታወረው ልባችንም እንዲበራ እንደ መጻጕዕ ቦታችንን ሳንለቅ እግዚአብሔርን በተስፋ መጠበቅ እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው።
ሰላም በማጣትና በጽኑ ሕመም ውስጥ ላለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ የምሕረት ዘመን ያምጣልን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
በመ/ር ሽፈራው እንደሻው