“ምኩራብ”
“እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ፤ የቤትህ ቅንዓት በላኝ።” (መዝ. 68፥9፤ ዮሐ. 2፥17)
የዐቢይ ፆም ሦስተኛው ሰንበት (እሑድ) ምኩራብ ይባላል፦ ስያሜውን ያገኘው ጌታችን በአይሁድ ቤተ-መቅደስ ተገኝቶ ቤተ-መቅደስ ንጹህ የእግዚአብሔር ቤት፣ የጸሎት ቤት፣ ሃይማኖትና ጽድቅ የሚነገርበት የተቀደሰ/የተለየ ቦታ መሆኑን ያረጋገጠበት ስለሆነ ነው።
ሊቁም “ቦአ ኢየሱስ ምኩራቦሙ ለአይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት” በማለት ጌታችን ወደ ቤተመቅደሱ የገባ ክህደትና ዓለማዊነትን አስወግዶ ሃይማኖትና ጽድቅን ለማስተማር መሆኑን ያስረዳናል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይፋ የታወቀ የመጀመሪያ ተአምራቱን በመግለጥ በገሊላ ቃና ክብሩን ሲገልጥ ደቀ መዛሙርቱም ሆነ ሌሎች በእርሱ አምነዋል። በቅፍርናሆም ጥቂት ቀን ከተቀመጠ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ስለነበር በቀጥታ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በዘሩባቤል ዘመን ተሠርቶ በሄሮድስ ዕድሳት ወደ ተደረገለት ቤተ መቅደስ ሄዷል። በመቅደሱም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ሲያገኝ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ በማስወጣት የለዋጮችንም ገንዘብ በማፍሰስ ገበታዎቻቸውንም ገልብጧል፥ ርግብ ሻጪዎችንም፦ ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ሲል ደቀ መዛሙርቱ የቤትህ ቅናት ይበላኛል የሚለው ትዝ እንዳላቸው በመጽሐፉ ተጠቅሶ አግኝተነዋል።
በሦስተኛው ቀን የተገነባው ሕያውና ዘለዓለማዊ ቤተ መቅደስ ሲሆን፣ የ46 ዐመቱ የንግድ ቤት ፈርሷል!
አይሁድም ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? ባሉት ጊዜ፣ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ ሲላቸው፣ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ የነበረ፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት፤ እርሱ ግን ስለ ሕንጻው ሳይሆን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስነት ሲነግራቸው ነበር። እርሱ በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሥቶ ሕያውና ዘለዓለማዊ ቤተ መቅደሱ ሲገነባ፣ ለዕድሳት 46 ዓመት የፈጀ የእነርሱ ቤት ግን እንደተነበየው በ70 ዓ∙ም በሮማውያን እጅ እንደፈረሰ ሊቃውንት ይመሰክራሉ።
በሦስተኛው ቀን የተገነባው ሕያውና ዘለዓለማዊ ቤተ መቅደስ የክርስቶስ ሰውነት(አካል) ነው።
ቤቱ የንግድ ቤት አድርገውት እንደነበረ በመጽሐፉ ተገልጿል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ብሎ ቤቱ የጸሎት እንጂ የንግድ ቤት እንዳልሆነ ሲነግራቸው በሌላ በኩልም አማናዊ መቅደስ እርሱ ራሱ እንደሆነ ሳይናገራቸው አላለፈም። ለዚህም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” (ዮሐ 3:21) በማለት ያረጋግጥልናል። በተጨማሪም “ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። (ራእ 21÷22-23) ሲል አሁንም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ ያየው ጽፎልናል። በሌላ በኩልም ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለሆነች ሕያውና ዘለዓለማዊት ናት።
ለእግዚአብሔር ቤት ልባዊ ቅናት ይኑረን!
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ሲል በመቅደሱ የነበሩትን የሥጋ ሥራዎችን ሁሉ እንዳስወገደ፣ አሁንም ከቤተ መቅደሱ የማያስፈልጉትን ሁሉ በጊዜው ማስወገድ ያስፈልጋል። ቤተ-መቅደሱን እርሱ ብቻ ይንገሥበት። ቤቱ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ስለሆነ አለማመን፣ ጥርጥር፣ ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፣ ክህደት፣መገዳደል፣ ሐሜት ትምክህት ወዘተ ከቅዱስ ቤቱ ተወግደው ቤተ መቅደሱ ንጹሕ አምልኮ፣ ምስጋናና ጸሎት የሚቀርብበት ሊሆን ይገባል። እንዲሁም በቅዱስ ቤቱ ፍቅር፥ ይቅርታ፣ ደስታ፥ ሰላም፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውኃት፥ ራስን መግዛትና ርህራሄም ሊነግሥ ይገባል።
ከዚህም ጋር አማኞች ሁላችን በሥጋችን እግዚአብሔርን ማክበር አለብን። የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም። የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ደግሞ ንጹሕ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔርን በሥጋችን ማክበር አለብን። ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “የግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።” በማለት ይመክረናል (1ቆሮ. 3፥16-17፤ 6:19-20)።
በሁለመናችን አምላካችንን አክብረን እንደ ፈቃዱ እንድንኖር እርሱ ይርዳን!
በመ/ር ኪደ ዜናዊ