ቅድስት ( የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት )

ትርጉም

የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ቅድስት ይባላል፤ ትርጓሜውም የተቀደሰች የተለየች ማለት ነው። ስያሜውም የተገኘው ከቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስለ ቅድስና በሰፊው ትምህርት ይሰጣል፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴው በሚካሄድበት ጊዜም የሚሰበከው ምስባክ፣ የሚነበቡ መልዕክታት፣ የሐዋርያት ሥራና ወንጌል ስለ ቅድስና የሚያስተምሩና የሚሰብኩ ናቸው፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ በዚህ ሳምንት፦ ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ ቅድስና፣ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ቤዛ ሆኖ በደሙ ሊቀድሰን እንደሆነና እኛም በቅድስና ሕይወት መመላለስ እንደሚኖርብን በሰፊው የሚሰበክበት ነው።

ሀ. እግዚአብሔር በባሕርይው ቅዱስ ነው፦

እግዚአብሔር በባሕርይው ቅዱስ ነው፤ ቅዱስ ማለት ልዩ፣ ክቡር ማለት ሲሆን የእርሱ ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትም የእግዚአብሔርን የባሕርይ ቅድስና ደጋግመው የመሰከሩ ሲሆን “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እየተባለም ይመሰገናል ( ኢሳ 6፥1-3 )።

እኛም ዕለት ዕለት “ይትቀደስ ስምከ፤ ስምህ ይቀደስ” የምንለው በባሕርይው ቅዱስ ስለሆነ ነው። የቅድስና ምንጭ እና ቅድስናን የሚሰጥም እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ለ. ክርስቶስ ወደ ዚህ ምድር የመጣው ለእኛ ቤዛ ሆኖ በደሙ ሊቀድሰን ነው ፦

በተነገረው ትንቢት መሠረት ዘመኑ ሲደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በከበረ ደሙ ዋጀን፤ ከበደላችን አነጻን፡፡ ቅዱሱ መጽሐፉም ” ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” (1ኛ ዮሐ1፥7) በማለት ይህንን እውነት ያረጋግጥልናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የበደል ስርየትን ያገኘነው በክርስቶስ ቤዛነት መሆኑን በኤፌሶን መልእክት እንዲህ ሲል ጠቅሷል። ” በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት” (ኤፌሶን 1፥7)።

ሐ. በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ተጠርተናል ፦

” ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ” (1ኛ ጴጥ 1፥15-16) ተብሎ በተጻፈው መሠረት በቅድስና ሕይወት የመመላለስና የመኖር መንፈሳዊ ግዴታ አለብን።

ቅዱስ ጳውሎስ “ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና” (1ኛ ተሰ4፥7) በማለት ተናግሯል። ስለሆነም የተጠራነው ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፣ ለሞት ሳይሆን ለሕይወት፣ ለውርደት ሳይሆን ለክብር መሆኑን ለአፍታ እንኳን መዘንጋት የለብንም።

እግዚአብሔር አምላካችን በሰውነታችን ኃጢአትንና ዐመፃን እንድናደርግ አልፈቀደልንም። “እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ” (ሮሜ 6፥12-13) በማለት ኃጢአትንና ዐመፃን እንድንጸየፍ ታዘናል።

ሐዋርያው በገላቲያ መልእክት ላይ እንደጠቀሰው የሥጋ ሥራ ተብለው ከተገለጡት ከዝሙት፣ ከርኵሰት፣ ከመዳራት፣ ጣዖትን ከማምለክ፣ ከምዋርት፣ ከጥል፣ ከክርክር፣ ከቅንዓት፣ ከቁጣ፣ ከአድመኛነት፣ ከመለያየት፣ ከምቀኝነት፣ ከመግደል፣ ከስካር ወዘተ (ገላ 5፥19) ከመሳሰሉት ርኩሰቶች ፈጽመን መለየት እንዳለብን በአጽንኦት መልእክት አስተላልፏል።

በአንጻሩ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ( ገላ 5፥22) በክርስትና ሕይወታችን ዘወትር መገለጥ እንዳለባቸው ተናግሯል።

በመጨረሻም የተጠራነው በቅድስና ሕይወት እንድንኖር መሆኑን አውቀንና ተረድተን ዘወትር በጽኑ እምነትና በንስሐ ሕይወት ልንኖር ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ