“የወንጌል አገልግሎትን በማስቀደም ዘመኑን የዋጀ ሥራ ልንሠራ ይገባል” …ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አድንቀዋል።
ክፍለ ከተማው ያከናወናቸውን ሥራዎች እና የገጠሙትን ተግዳሮት በመጽሔት አሳትሞ ለአድባራቱና ለገዳማቱ ለንባብ ማብቃቱም ለቀጣይ ሥራዎች ትልቅ መነሣሣትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን በበጀት ዓመቱ ያሳዩት ቆራጥ አመራር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት ድረስ በመሄድ የአሠራር ሂደቱን በተለያያ ጊዜ እንደተመለከቱም ጠቅሰዋል።
በወንጌል አገልግሎት እና በልማት በኩል ጥሩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም በሰሜኑ ክፍል በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ወገኖች ክፍለ ከተማው ዕርዳታ ማድረጉ መንፈሳዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የሚገልጽ ነው ብለዋል።
ሁሉም የቤተክርስቲያን አገልጋይ በንቃትና በሥራ ወዳድነት መንፈስ ኃላፊነቱን ከተወጣ በቤተክርስቲያን ላይ የሚታየውን የሥራ ክፍተትና የሚሰነዘረውን ትችት ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።
ለዚህም ደግሞ የወንጌል አገልግሎትን በማስቀደም ዘመኑን የዋጀ ሥራ ልንሠራ ይገባል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ክፍለ ከተማው የተፈናቀሉትንና የተጎዱትን የመርዳት መርሐግብርንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አክለውም ወደፊት ክፍለ ከተማው በሁሉም በተሰጡት የሥራ መስኮች የበለጡ ሥራዎችን በትጋት እንዲያከናውን አሳስበዋል።
ሌሎቹም ክፍላተ ከተማ ከቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት በመማር የተጎዱትን እንዲያግዙ አጽንኦት ሰጥተው መልእክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም በቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት ከክፍለ ከተማው ጋር ተናበው ላስመዘገቡት ውጤት ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-
1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
4. Twitter.com/AddisDiocese