ሰው በመገደሉና በዓሉ በተገቢው ባለመከበሩ መንግሥት በጥልቅ ማዘኑን ይገልጻል…የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ኢትዮጵያ በዓለም ደምቃ እንድትታይ ከሚያደርጓት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል።
በበዓለ ጥምቀቱ የታዩት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ዕሴቶች በዓሉ የኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀ ውብ አብሮነትንም ለዓለም ያሳየ ሆኗል።
በዓሉ የኢትዮጵያውያንን መፋቀር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም በሚገልጽ መንገድ እንዳይከበር የተለያዩ አካላት የሸረቧቸውን ሤራዎች ሕዝቡና የጸጥታ አካላት ተናብበውና ተቀናጅተው አክሽፈውታል።
ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች ከፊታችን አሉ። እነዚህ ክንውኖች እንዳይሳኩ የኢትዮጵያን ገጽታ ማበላሸት የፈለጉ አካላት የጥምቀትን በዓል በመረበሽ ተልኳቸውን ለማሳካት ሞክረው ነበር፣ ነገር ግን አልተሳካላቸውም።
የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው የመጡት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የማኅበራዊ መስተጋብሩ አካል በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው በዓሉን አድምቀዋል።
የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለቱሪዝም መስሕብነትና ኢትዮጵያን ለዓለም በማሳየት ታላቅ ሚና አለው። በዚህም የተነሣ ከበዓሉ ቀደም ብሎ በተደረገ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው መስተዳድር አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና ወጣቶች በጋራ በመሥራት በዓሉ በአብዛኛው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ተችሏል።
የጥምቀት በዓል በመላ ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ ቢከበርም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይ ብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።
በዓሉ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ፣ እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን ይገልፃል። መንግሥት በስፍራው የተፈጠረውን ክሥተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ ያስታውቃል።
ለዘመናት የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብራችን ማሳያ በሆኑ እንደ ጥምቀት በዓል ያሉ ሀብቶቻችንን ለማደብዘዝ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር ይከሽፋል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል።
በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese