በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል!
በተለምዶ መሿኪያ ተብሎ በሚጠራው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት አከባቢ በሚገኘው የታቦት ማደሪያ ስፍራ ከአስራ ሰባት አድባራትና ገዳማት የወጡ ታቦታት አድረዋል።
እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን ከዋዜማው ጀምሮ በስፍራው ተገኝተው ሌሊት ማኅሌቱን፣ ንጋት ላይ ደግሞ ሥርዓተ ቅዳሴውንና ትምህርተ ወንጌል ተከታትለዋል።
ከቅዳሴው መርሐግብር በኋላ በመ/ሃ ተስፋዬ ሞሲሳ በዓሉን የተመለከተ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል።
በዓሉ ትህትና የተፈጸመበት፣ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት (ማቴ 3፥16-17)፣ ጽድቅ የተፈጸመበት (ማቴ 3፥15) መሆኑን አብራርተዋል።
ምእመናን በሙሉ የክብረ በዓሉን መልእክት በመረዳት እንዲያከብሩም አሳስበዋል።
የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ኅ ዳዊት ታደሰ የዘንድሮው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለየት ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምእመናን መገኘታቸው፣ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ከክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከአባቶች፣ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጋር በቅርበት በመመካከርና በመነጋገር በሰላምና በፍቅር እየተከበረ መገኘቱ ለየት እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
ክርስቶስ በጥምቀቱ ሁላችንንም አንድ ያደረገበትና ትህትና ከፍቅር ጋር የተገለጠበት በዓል መሆኑን አብራርተዋል።
የዘረኝነት፣ የመለያያት፣ የክፋት፣ የተንኮልና የምቀኝነት ሃሳብ የተወገደበት በዓል መሆኑንም አያይዘውም አውስተዋል።
በተያያዘም ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በስፍራው መብራት በተደጋጋሚ መጥፋቱን ገልጸው የክፍለከተማው የመብራት ኃይል አገልግሎት ወደፊት እንዲህ ያለውን ስህተት እንዲያርም አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese