የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይሜኖት ወልዱ የዘውዲቱ መሸሻ የህጻናትና ቤተሰብ የበጎ አድራጎትና ልማት ማሕበር ጎበኙ።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይሜኖት ወልዱ በሽሮ ሜዳ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው የዘውዲቱ መሸሻ የህጻናትና ቤተሰብ የበጎ አድራጎትና ልማት ማሕበር ጎብኝተዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቋሙን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢጎድል ምን ይጠቅመዋል?” ማቴ 16፥26 የሚል የእግዚአብሔር ቃል መነሻ አድርገው አስተምረዋል።
የሰው ልጅ የዕውቀት፥ የገንዘብ፥ የጉልበት እና የተለያዩ ሥጦታዎች ባዕለ ጸጋ የሚሆነው ለሌሎች እንዲያካፍል መሆኑን የገለጹት ክቡር ዋና ሥራ እስኪያጁ እምነታችን የምንተገብርበት የልግስና ዋጋ እና በዚህ ምክንያት የሚገኘው ሰማያዊ ክብር ታላቅ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ መሠረት የወዘሮ ዘውዲቱ የሕጻናት ማሳደጊያ ተቋም ልጆችን የሚያሳድገው በዕውቀት የተመሠረተ መንፈሳዊነትና ሥነ ምግባር መሆኑን በመመልከት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ ሰውን በመልካምና በበጎ ሕይወት የሚያሳድግ መሆኑን ተገንዝበው ደስታቸውን በመግለጽ ካህናትና ምእመናን የወ/ሮ ዘውዲቱን መሰል ሥራዎች በመሥራት በመልካሙ ሁሉ እንዲሳተፉና ተቋሙን እንዲደግፉ በማሳሰብ የበጎ አድራጎቱን ተካፋይ በመሆን ለተቋሙ ስጦታ አበርክተዋል።
የዘውዲቱ መሸሻ የህጻናትና ቤተሰብ የበጎ አድራጎትና ልማት ማሕበር በ1984 ዓ/ም በወ/ሮ ዘውዲቱ መልካም ፈቃድና ለበጎ አድራጎት ያላቸውን ተነሳሽነት መሠረት በማድረግ ቤት ንብረታቸውን በመሸጥ የተመሠረተ ሲሆን፣ ማሕበሩ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጅ አልባ የሆኑት ሕጻናት በማሳደግ የሚያስተምር ነው።
በዚህ መሠረት ተቋሙ በ30 ዓመት ውስጥ ከ48 በላይ ሕጻናት አሳድጎ በተለያየ የትምህርት ዘርፍና ደረጃ በማስተማር ማስመረቁን ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ከ22 በላይ በማሕበሩ አድገው ትዳር መሥርተው መውጣታቸውን ተገልጻል።
ማሕበሩ በአሁን ሰዓት 60 ህጻናት በግቢው ውስጥ፥ 35 ሕጻናት ከግቢው ውጭ እያሳደገ እንደሚገኝ ታውቋል።
የማሕበሩ መሥራችና ባለ ራዕይ የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ መሸሻ ለማኝ የሚል ነገር ከሀገራችን እንዲጠፋ ማድረግ አለብን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ይሁን እንጂ ማሕበሩ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ ስለሌለው ምእመናን ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
ስለዚህ በዚህ የተቀደሰና በጎ ሥራ መሳተፍ ለምትፈልጉ ሁሉ ከታች በተቀመጠ አድራሻ መሠረት መሳተፍ እንደምትችሉ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።
ስልክ ቁጥር- 0906640754
የባንክ ሒሳብ-C/A- 1000004338573
በመ/ር ኪደ ዜናዊ
ምንጭ፡ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese