የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 15,000,000 ብር የሚገመት የአልባሳት፣ የአስቤዛ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ!

የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት አብያተክርስቲያናትን በማስተባበር 15,000,000 ብር የሚገመት የአልባሳት፣ የአስቤዛ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍን በማሰባሰብ በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ አደረገ።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ብ ሩፋኤል የማነብርሃን የዕርዳታውን ዓላማ እና አሰባሰብ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዕርዳታው ዋና ዓላማ በሀገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከሞቀ ቤታቸውና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ወገኖች የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።

ዕርዳታው ከቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል፣ ከቦሌ ኆ/ብ ቅድስት ማርያም፣ ከቦሌ ቡልቡላ ደ/መ/መድኃኔዓለም፣ ከገርጂ ደ/ገ/ቅ/ጊዮርጊስ፣ ከቦሌ ቡልቡላ ፍ/ሕ ቅድስት ማርያም እና ከም/ሰ ወደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል እና ቅ/አርሴማ ቤተክርስቲያን ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ኮሚቴ ተዋቅሮ ዕርዳታው ከምእመናን መሰብሰቡንም አውስተዋል።

አያይዘውም ከዚህ በፊት የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ዕርዳታ ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው እና ከክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት በመነጋገር ለተጎዱት ወገኖች ድጋፉ መሰብሰቡንም ጠቅሰዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ከክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በዕርዳታ ጉዳዮች ተናቦ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የተሰበሰበውን አልባሳት፣ አስቤዛ እና ቁሳቁስ የጫኑት መኪናዎችም በነገው ዕለት ወደ ተጎዱት ወገኖች እንደሚጓዙ የተናገሩ ሲሆን የዕርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችም ወደ ስፍራው እንደሚሄዱ ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ “( ሮሜ 12:15) የሚለውን መለኮታዊ ቃል አንስተው መልእክት አስተላልፈዋል።

የሰዎችን ደስታ እንደምንጋራ ሁሉ ኃዘናቸውንም ልንጋራ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ጦርነትን እንደማትደግፍ ገልጸው፤ በሀገራችን የተከሰተው ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እየጸለይን በጦርነቱ የተጎዱትን ወገኖች እንረዳለን ብለዋል።

የተራቡትን መመገብ የተጠማውን ማጠጣት የተቸገረውን መርዳት የዜግነት፣የሃይማኖት እና የሰባዊነት ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሀገረ ስብከቱ ጦርነቱ በተከሰተ ጊዜ 15,000,000 ብር ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ ማድረጉን አውስተዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ከክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ያደረገውን ዕርዳታ አድንቀው ለሌሎች ክፍላተ ከተማ አርአያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ብፁዕነታቸው 15,000,000 ብር የሚገመተውን የአልባሳት፣ የአስቤዛ እና የቁሳቁስ ድጋፍ የሚገልጽ ሰነድ ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው አስረክበዋል።

የተሰበሰበው ዕርዳታ በጣም ለተጎዱት እና በብዙ ስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በአግባቡ እንዲደርስ አባታዊ መልእክታቸውን በአጽንኦት አስተላልፈዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው የተሰበሰበው ዕርዳታ ብዙ መስዋዕት የተከፈለበት መሆኑን ጠቅሰው ከልብ አመስግነዋል።

መርሐግብሩ የተካሄደው በቦሌ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ነው።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese