የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ያካሄደውን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎች!
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ት ወንድወሰን ገ/ሥላሴ “የ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ ሪፖርትን” ለጉባኤው አቅርበዋል።
ሪፖርቱ በሰበካ ጉባኤ፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በሂሳብና በጀት፣ በቁጥጥር፣በሰንበት ት/ቤት፣ በትምህርትና ሥልጠና፣ በዕቅድና ልማት፣ በቅርሳ ቅርስ እና በምግባረ ሠናይ ክፍሎች የተከናወኑ ሥራዎችን ያካካተ ነበር።
በበጀት ዓመቱ ክፍለ ከተማው አብዛኞቹን ዕቅዶች በሥራ ላይ እንዳዋለ ከሪፖርቱ ተደምጧል።
የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የክፍለ ከተማውን የአሠራር ሂደት በተለያያ ጊዜ በቢሮም ሆነ በመስክ ተገኝተው በመጎብኘትና አመራር በመስጠት ያደረጉት አስተዋጽኦ ለክፍለ ከተማው ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተገልጿል።
የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ሠራተኞች በፍቅር፣በመግባባትና በመወያየት ሥራዎቻቸውን መሥራታቸው በመልካም ገጽታ ተነሥቷል።
የብዙኃን አድባራትና ገዳማት ሁለንተናዊ እድገትና የሥራ ትብብር መኖር ለክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሥራ መሳለጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ተጠቅሷል።
በክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት ሥር 41 የሚሆኑ አድባራትና ገዳማት እንደሚገኙም ተገልጿል።
በተያያዘም በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክፍለ ከተማው የሰላምና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገበያው ቤተክርስቲያን ሰላምን በመስበክ፣ ከኮሮና ጋርም በተያያዘ ምእመኑ ራሱን እንዲጠብቅ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎችን እየሠራች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
ወደፊት የሚከበሩት የልደትና የጥምቀት በዓላት ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ያለ ስጋት እንዲከበሩ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በአግባቡ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ በአጽንኦት ተናግረዋል።
አያይዘውም የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት በሰላምና ጸጥታ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማው ቤተክህነት በመንፈሳዊ አገልግሎት እና በልማት ሥራ በኩል ውጤት ላስመዘገቡት አድባራትና ገዳማት ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ደረጃ በማውጣት የሽልማት ስጦታ እና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ለክፍለ ከተማው የፖሊስ መምሪያ በተጨማሪም ለክፍለ ከተማው የጸጥታ እና የሰላም ቢሮ ኃላፊ የምስክርና የሽልማት ወረቀት ተሰጥቷል።
የሽልማት አዘጋጅ ኮሚቴው ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ት ወንድወሰን ገ/ሥላሴ ስጦታን አበርክቶላቸዋል።
አጠቃላይ መርሐ ግብሩን ሊ/ኅ አብርሃም አባተ የክፍለ ከተማው ቤተክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ኃላፊ መርተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያሬዳዊ ዝማሬ እና ቅኔ አቅርበዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ መርሐ ግብሩ ባማረ መልኩ እንዲዘጋጅ ትብብር ያደረጉትንና የታደሙትን በሙሉ አመስግነዋል።
በመጨረሻም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ጉ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ መመሪያዎችን አስተላልፈው ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ጉ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ት ወንድወሰን ገ/ሥላሴ፣ የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች፣ በክፍለ ከተማው ሥር የሚገኙ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የአስተዳደር ሠራተኞት፣ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች እና የክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ