የሰሜን አሜሪካ ማኀበረ ካህናት ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ዘረፈ ብዙ አገልግሎት እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ!!!
በሰሜን አሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ ካህናት “የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት ” በሚል ኅብረት መሥርተው ሀገራቸውና ቤተክርስቲያናቸውን በሁለንተናዊ መልኩ እያገለገሉ ይገኛሉ።
ማኅበሩ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ለተጎዱ ካህናትን ምዕመናን ዕርዳታ ለማድረግ ያሰባሰበውን ገንዘብ በአግባቡ ለተጎጂዎች በማሰራጨት የፕሮጀክቱን መዝጊያ ሥነ ሥርዓት እንዲሁም ወቅታዊው የሀገራችንንና የቤተ ክርስቲያንን ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጀውን መርሐ ግብር ታኅሣሥ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በአትላንታ ጉባኤውን አካሒዷል።
በዚህ ጉባኤ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚና ሥራ አመራር እንዲሁም የአትላንታ ማኅበረ ካህናት አባላት በጉባኤው በአካል የተገኙ ሲሆን የማኅበረ ካህናቱ አባላትና የተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች በዙም ጉባኤውን ተካፍለዋል።
በጉባኤው የኦሮሚያው ፕሮጀክት ጠቅላላ የሥራ አፈጻጸም ሪፓርትና የፋይናንስ ሪፓርት በዝርዝር ቀርቧል፣በከፍተኛ ችግር ለነበሩ ከሦስት ሺህ አራት መቶ በላይ ለሆነ ቤተሰብ የተደረገውን ድጋፍ አፈፃጸም ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክና ከCCRDA የቀረበውን የሒሳብ ሰነድ በሕጋዊ ማስረጃ ተመልከቷል።
አድራሻቸው ባለመገኘቱ የተነሣ በጀት ተይዞላቸው ዕርዳታው ያልደረሳቸው ከ175 በላይ ወገኖች መኖራቸው ተገልጾ ወደፊት የማፈላለግና የማዳረስ የማዳረስ ተግባሩ ይቀጥላል ተብሏል።
ገንዘቡን በማሰባሰብ ከፍተኛ ወገናዊ ግዴታውን የተወጣው መምህር ዘመድኩን በቀለ በጉባዔው ላይ በዙም ተገኝቶ በቀረበው ሪፖርት ደስ መሰኘቱን ገልጿል፣ ጉባዔውም መ/ር ዘመድኩን በቀለ ላደረገው አስተዋጽዖ ምስጋናውን አቅርቧል።
በተጨማሪም “የሀገራችንና የቤተክርስቲያንን ወቅታዊ ሁኔታና የካህናቱ ድርሻ” በሚል የመወያያ ጽሑፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተርደርጓል።
በውይይቱም መሠረት በተፈጠረው ሀገራዊ ችግር ቤተ ክርስቲያን በብዙ መልኩ የተጎዳች በመሆኑ ካህናቱና ቤተሰቦቻቸው አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑም ታምኖበት ሁሉም የማኀበረ ካህናቱ አባላት እንደ አባል ልዩ መዋጮ እንዲያዋጡ ወሳኔ አግቷኝል።
በተያያዘ ዜናም ማኅበሩም በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ላይ ለከረሙት ለላሊበላ ደብር ካህናት አንድ ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር እንዲሰጥ ወስኗል።
ጉባኤው ወደፊትም ማኅበሩ የቤተክርስቲያንን መዋቅር ለማጠንከር በጋራ መሥራትና በአባላቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በተሻለ መልኩ ማቀራረብ እንደሚገባ አውስቶ በአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ስለ ሀገር ምሕላ በማድረስ ተጠናቋል።
የመረጃው ምንጭ:- የማኅበሩ የፌስቡክ ገጽ
በመ/ር ሽፈራው እንደሻው