የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት የዕድሳት ሥራ የሳይት ርክክብ ተካሄደ!!!

በዘመናዊ መልኩ ታድሶ ለአገልግሎት ምቹ የማድረግ ሥራ የተጀመረው የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ዝርዝር ጥናቶችን እንዲያጠና በተሰየመው ኮሚቴ አማካኝነት የቅድመ ግንባታ ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።

የጥናት ኮሚቴው የጥምቀት በዓልን መቃረብ ተከትሎ የግንባታ ሥራው በአስቸኳይ እንዲጀመር ማድረግ እንዲቻልና ለግንባታ ሥራው መፋጠን ይረዳ ዘንድ የግብዣ ጨረታ እንዲወጣ የሚቻልበትን ሁኔታን ማመቻቸት እንደሚገባ መክሯል።

የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን አሸናፊ ድርጅቱ የበዓሉን መቃረብ፣የግንባታ ሥራውን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በጊዜ የለም እሳቤ ሌት ተቀን በገባው ውል መሠረት በመሥራት የግንባታ ሥራው ተጠናቆ ለበዓሉ እንዲደርስ ብርቱ ጥረት ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የሕንፃ ሥራ ተቋራጩም በበኩላቸው ይህን ታሪካዊ ሥፍራ የመገንባት ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው የግንባታ ሥራውን በተቻለ ፍጥነት ሌት ተቀን በመሥራት ለበዓሉ ለማድረስ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣የግንባታ ሥራውን የሚያስተባብረው ኮሚቴ አባላት እና ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመ/ር ሽፈራው እንደሻው