የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ተከብሮ ዋለ!

የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በጉራጌ ሀገረ ስብከት ስር በሚገኘው ቆጠር ገድራ መካነ ቅዱሳን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት እና አቡነ ሀብተማርያም አንድነት ገዳም አዳሪ መንፈሳዊ ት/ቤት ተከብሮ ውሏል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ክብረ በዓሉን የተመለከተ ትምህርት ሰጥተዋል።

ጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸምና በመከተል መልካም ፍሬ አፍርተው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉ አባት መሆናቸውን አውስተዋል።

አያይዘውም እኛም በዘመናችን በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር በመጓዝ እንደ አባቶቻችን መልካም ፍሬ ማፍራት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ብፅዕነታቸው በገዳሙ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚገኙትን ደቀ መዛሙርትንም ጎብኝተዋል።

በገዳሙ ውስጥ በቁጥር 60 የሚሆኑ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የቅዳሴና የመጻሕፍት ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

ደቀ መዛሙርቱ ነገ የሚጠበቅባቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ዛሬ ትምህርታቸውን በአጽንኦት መከታተል እንዳለባቸው ብፁዕነታቸው መክረዋል።

አያይዘውም በሰሜኑ ክፍል በስፋት የሚሰጠውን የአብነት ትምህርት በደቡቡ ክፍልም ለማሳደግ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ብፁዕነታቸው ከዚህ በፊት በገዳሙ ውስጥ ምንኩስናን ለሰጧቸው መነኮሳት ስለ ምንኩስና ምንነት ሰፊ ጥናት እንዲያጠኑ ያዘዟቸው ሲሆን መነኮሳቱም የተሰጣቸውን ጥናት አጥንተው ለብፁዕነታቸው አቅርበዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ር ኤልሳ ናርዶስ ለብፁዕነታቸው እና በበዓሉ ላይ ለተገኙት ሁሉ “የእንኳን በሰላም መጣችሁ” መልእክት አስተላልፈዋል።

በገዳሙ የሚማሩትን የደቀ መዛሙርት ቁጥር ከፍ ለማድረግ ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ አካል ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው አስተዳዳሪው አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

በገዳሙ በክብ ቅርፅ እየተሠራ ያለው ትልቅ ሕንጻ ቤተክርስቲያንም ወደ 60 ፐርሰንት መድረሱን ጠቅሰዋል።

በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሐት ሣህሉ ተሰማ ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ መ/ር ኤልሳ ናርዶስ፣ የሀገረ ስብከቱና የወረዳው ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እና ምእመናን ተገኝተዋል።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ