የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አራተኛ በዓለ ሲመት በድምቀት ተከብሮ ዋለ

የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ አራተኛ በዓለ ሲመት በወልቂጤ ከተማ በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ካቴድራል በድምቀት ተከብሮ ዋለ።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ባስተላለፉት መልእክት በዓሉ የአንድ መንፈሳዊ አባት በዓል ሳይሆን የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለበርካታ ዘመናት ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን በሚመጡ ጳጳሳት ስትተዳደር እንደነበር አውስተዋል።
ይህም ለቤተክርስቲያን በተለይ አገልግሎትንና ወንጌልን በሰፊው ለማዳረስ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የራሷን ጳጳሳት መሾም ከጀመረች በኋላ ምእመናንን በሀገሪቱ ቋንቋዎች ማስተማርና ማገልገል ችላለች ብለዋል።
ጳጳሳት የቤተክርስቲያን አምባሳደሮች፣ የእግዚአብሔር እንደራሴዎችና የአገልግሎት መሪዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
ጳጳሳት አብያተክርስቲያናትን ባርከው ለአገልግሎት ያበቃሉ፣ዲያቆናትንና ካህናትን ይሾማሉ፣ የቤተክርስቲያንን ምሥጢራት ይፈጽማሉ በማለት አብራርተዋል።
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ሰ ሳህሉ ብፁዕነታቸው በአራት ዓመት ውስጥ በሀገረ ስብከቱ ያከናወኗቸውን በርካታ ሥራዎች በሪፖርት አቅርበዋል።
ስብከተ ወንጌልን እንዳስፋፍ፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ግንባታን እንዳስጀመሩ፣ በመንበረ ጵጵስና ግቢ ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎች እንዲገነቡ ማድረጋቸውን፣ አዲስ የተሠሩ አብያተክርስቲያናትን ባርከው ለአገልግሎት እንዳበቁ፣ የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም እንደሠሩ ከሪፖርቱ ተደምጧል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ብፁዕነታቸው በጥቂት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያከናወኗቸውን ሥራዎች ጠቅሰዋል።
በሀገረ ስብከቱ ዘመናዊ አሠራርን በመዘርጋት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ የካርታ ይዞታ የሌላቸውን አብያተክርስቲያናት የካርታ ይዞታ እንዲያገኙ ማድረጋቸውንና የልማት ሥራዎችን በማፋጠን በኩል ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አብራርተዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ብፁዕነታቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ በኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ በዞኑ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ገልጸዋል።
የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎችን በፍቅር በመያዝና በዞኑ የጸጥታ ጉዳይ ላይ ግንባር ቀደም በመሆን ለከተማዋ እድገት ጉልህ ሚና አበርክተዋል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊም ብፁዕነታቸው መልካም አባት፣ የሃይማኖት አባትና የልማት አርበኛ ናቸው በማለት ጠቅሰዋል።
ብፁዕነታቸው በመልካም አስተዳደር በኩል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባና ከጉራጌ አህጉረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያከናውኑበት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣የወልቂጤ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን ተገኝተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
የዜናው ምንጭ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ