“አስከፊ የኑሮ ሁኔታና ቅንነት ከጎደለው የካራን አስተሳሰብ ወጥተን የዕረፍት ምድራችን ወደ ሆነችው ከነዓን እንግባ“…ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ
የአጋዕዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በርካታ አገልጋዮችና ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናን በተገኙበት ተከብሮ ውሏል፡፡
በአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጋባዥነት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዘዳንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ፊልጶስ የዕለቱን ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
በትምህርታቸውም የእምነት አርበኛ የሆነውን የአብርሃምን የጥሪ ሕይወት: ለጠራው እግዚአብሔር የታመነበትን መንገድ እና በመታዘዙ የተነሣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለውን የእምነት ፍሬ አብራርተዋል፡፡
አያይዘው ዓለማችን በክፋትና በባዕድ አምልኮ ተሞልቷል፡የቀደመችውን ካራንንም መስሏል፡ ስለዚህ አስከፊ የኑሮ ሁኔታና ቅንነት ከጎደለበት የካራን አስተሳሰብ ወጥተን የዕረፍት ምድራችን ወደ ሆነችው ከነዓን እንግባ ብለዋል፡፡
የካቴድራሉን ሕንፃ ዕድሳት በሚያጠናው ፋሲል ጊዮርጊስ በተባለው የአርክቴክት ድርጅት እና በቴክኒክ ኮሚቴ አባላት አማካኝነት ተጠንቶ የተደረሰበትን የጥናት ግኝት በካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ሽታው ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በቀረበው የጥናት ሪፖርት የካቴድራሉን ታሪካዊና ትውፊታዊ ይዘት በጠበቀ መልኩ እንዲታደስ ቅድመ ዕድሳት የሚያስፈልገው ሁሉ ተጠንቶና አዲስ ፕላን ተዘጋጅቶ ዘጠና አምስት በመቶ (95%) መድረሱም ተገልጿል፡:
የጥናቱን መጠናቀቅ ተከትሎ በመስከረም ወር ዕድሳት እንደሚጀመርና ከዕድሳቱ በኀላም ለሚቀጥሉት 80 ዓመታት ያክል ያለምንም ችግር አገልግሎት እንደሚሰጥ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ያለምንም ክፍያ ለጉልበታቸውና ጊዜያቸው ሳይሰስቱ በበጎ ፈቃድ የሕንፃ ቴክኒክ ኮሚቴ በመሆን አገልግሎት በመስጠት የሚገኙት በዘርፉ ከፍተኛ ሙያ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆናቸውን የደብሩ ሰ/ጉ/ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዕለቱ የእምነት ጥንካሬ የተፈተሸበት፡ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ምን ያክል ቅርብ መሆኑን የተረዳንበት ነው ብለዋል፡፡
በሕንፃ ዕድሳቱ ቴክኒክ ኮሚቴ እና በጥናት ድርጅቱ ሲጠና ቆይቶ የቀረበልን የጥናት ግኝት ሪፖርት ምን ያክል እንደ ደከሙ አመላካች መሆኑን ገልጸው ፡ በዚህ ታሪካዊ ሥራ ላይ በገንዘብ፡ በሐሳብ፡በጸሎትና በልዩ ልዩ ሙያ አስተዋጾኦ ያደረጉትንና የደከሙትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
አክለው የካቴድራሉ ሕንጻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የኪነ ሕንፃን ቀደምትነትና ታሪካዊነት ከማሳየቱም ባሻገር የብፁዓን ወቅዱሳን አባቶቻችን በዓለ ሲመት የሚከበርበት፡ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጥበት እንዲሁም ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ያለበት ትልቅ ቦታ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ዕድሳት ተደርጎለት አገልግሎት እንዲሰጥ ሁላችንም የቻላችሁት ሁሉ አድርጉ በማለት አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ ፡ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡ የሀገረ ስብከቱ ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ፡ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ምህረት በቃሉ ወርቅነህ፡ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሲራክ አድማሱ፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤ/ክህነት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና እንዲሁም በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ