“ምእመናን ልጆቻችን በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጡ በጣም መጠንቀቅ አለብን” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ምእመናን ልጆቻችን በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጡ በጣም መጠንቀቅ አለብን ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ገለጹ።
ቅዱስነታቸው ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት በዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን፣ በሕዝባችንና በደመ ክርስቶስ በተቀደሱ ክርስቲያን ልጆቻችን ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሰተ ስለሆነ ከምንም ጊዜ በላይ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀን ልንጸልይ፣ ልናለቅስና ልናዝን ይገባናል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ይህንን የፈተና ጊዜ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታ የምናልፈው ከሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠባሳ ታሪክ መሆኑ አይቀርም፤ በእግዚአብሔርም ተጠያቂነትን ማስከተሉ አይቀርም ብለዋል።
ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች፣ ምእመናንና ምእመናት ፈተና ላይ ሲወድቁና መከራ ሲጸናባቸው ቅዱስ ሲኖዶስን በቀጥታ የሚመለከተው ስለሆነ የመፍትሔው አካል ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል በማለት ገልጸዋል።
ይህ ጉባኤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጎዱ ለሚገኙት ምእመናንና ምእመናት እንደዚሁም በአጠቃላይ ያለ ፍትሕ እየተጎዱ ለሚገኙ ሰዎች መፍትሔ አምጪ አካል ሆኖ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ቅዱስ ፓትርያርኩ በመግለጫቸው የአሁኑ ጊዜ ከሌላው ጊዜ ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የችግሩ ክብደትና ውስብስብነት ማየሉ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
አያይዘውም የችግሩ ክብደቱን አይተን የምንሸሸው ሳይሆን የቤተክርስቲያናችን የውስጥ አቅምን በማየት የምእመናንን ትብብርና አገዛ በመጠየቅ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትንና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከራውንና ፈተናውን መቋቋም ይኖርብናል ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ለመንግስት፣ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት የአደራ መልእክት “የሁሉም ነገር መሠረትና የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ሲባል አስፈላጊ የሆነ ዋጋ መክፈል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን” አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም ዋስትና ያለው ሰላም በሀገራችን ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙርያ ተሰባስበው መወያየት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነትን መፈጸም ሲችሉ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ