የመረጃ ቴክኖሎጂ ትግበራ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

አሁን ባለንበት ዘመን የተቋማትን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ተቋማት ያሏቸውን የዕለት ተዕለት ተግባራት በአግባቡ ማከናወን የሚያስችሏቸውን የመረጃ መሠረተ-ልማቶች እና ሥርዓቶች በመገንባት ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት የሚችሉበትን ሁኔታ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

ከቴክኖሎጂው የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም እንዲቻል ተቋማዊ የቴክኖሎጂ አመራር ሥርዓት መፍጠር እንዲሁም የቴክኖሎጂ አደረጃጀት በአግባቡ መዘርጋት እና ለመዋቅሩ የሚመጥን እውቀት፣ ክህሎት፣ የትምህርት ደረጃ፣ ልምድ እና የመወዳደሪያ አቅም ያላቸውን አመራሮች እና ባለሙያዎች መመደብ ወሳኝ ነው፡፡

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አመራር ሰጪነት አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትና ሥርዓት እንዲዘረጋ እንዲሁም የሚዘረጋውን መሠረተ ልማትና ሥርዓት በአግባቡ በመጠቀም የሀገረ ስብከቱን የዕለት ተዕለት ተግባር በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ውጤታማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ የቴክኖሎጂ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ቴክኖሎጂ የአንድ ክፍል ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ተሳትፎ ውጤት እንደመሆኑ መጠን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ/አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ ነው፡፡
የመረጃ ቴክኖሎጂ/የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥራ አንዴ ተሠርቶ የሚያልቅ ሥራ ባለመሆኑ ሀገረ ስብከቱ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ ሰጭነትና መሪነት ወቅታዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን/ሲስተሞችን አዘጋጅቶ ሥራ ላይ አውሏል፡፡
ለተሠሩት ሲስተሞች ግብዓት የሚሆን የሰው ኃይል እና የንብረት ሀብት መረጃ የሚሰበስቡ ኮሚቴዎች አዋቅሮ ከ200 በላይ ገዳማትና አድባራት መረጃ ተሰብስቦ ሙሉ በሙሉ ወደ ማዘመን ሥራ ተግብቷል፡፡

በሀገረ ስብከቱ ከተሠሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥራዎች መካከል፡-

  1. የሰው ሀብት አስተዳደር ሲስተም/ Human Resource management system
  2. የንብረትና ሀብት አስተዳደር ሲስተም/ Asset Management System
  3. የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደር ሲስተም/Archive File Management system
  4. የአላቂ ዕቃዎች ዕቃዎች አስተዳደር ሲስተም/ Stock Management System
  5. ድረ ገጽ∕ ዌብ ሳይት፣ ማኅበራዊ ፌስ ቡክ ገጽ፣ዩትዮብ ቴሌግራም ቻናል/ Web site እና
  6. የሀገረ ስብከቱ ሕንፃ ኔትዎርክ ዝርጋታ፣
  7. የ27 ሜጋ ባይት ብሮድባንድ ኢንተርኔት እና ዋይ ፋይ (Wi- Fi) አገልግሎት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡
    እስከ አሁን በሀገረ ስብከቱ የተሠሩ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን የበለጠ ለማጠናከር በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልካም ፈቃድ በሀገረ ስብከቱ አይቲና ዶክሜንቴሽን ዋና ክፍል ሥር በበጎ ፈቃደኝነት ሙያዊ አገልግሎት የሚሰጥ የሀገረ ስብከቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መማክርት ኮሚቴ (IT Advisory Committee) በንግድ ሚኒስቴር፣ኢንሳ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ኢቴክ፣ኢሲኤ እና በግል መሥራያቤት የሚሠሩ 7 አባላት ያሉት የአይቲ ኤክስፐርቶችና ባለሙያዎች ያሉበት ዓቢይ ኮሚቴ ተዋቅሮ አጠቃላይ ሀገረ ስብከቱን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራር ለማዘመን ሌት ተቀን እየሠራ ይገኛል፡፡
    በአሁኑ ወቅት ሀገረ ስብከቱ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ያለውን አጠቃላይ መዋቅራዊ አደረጃጀት የሚያጠና 13 አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ የሀገረ ስብከቱን መልካም አስተዳደርን በአግባቡ እና በዘመናዊ መልኩ ማስፈን የሚያስችል ሥራ ለመሥራት እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ራሱን ለመቻል በዓይነቱ ልዩ የሆነ በአሮጌ ቄራ ባለ 3B + G+15 ሕንጻ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡