“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዋ የትምህርት ሚኒስቴር መሆኗ” ተገለጸ
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዋ የትምህርት ሚኒስተር ናት” ሲሉ ገለጹ።
ብፁዕነታቸው ይህንን የተናገሩት በቀን 13/9/2013 ዓ.ም በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ተሠርተው የተጠናቀቁትን G+1 እና G+4 ሕንጻዎችን በጸሎት በመረቁበት ዕለት ነው።
G+1 ሕንጻው ለቢሮ አገልግሎት የሚውል ሲሆን G+4 የሆነው ሕንጻ ደግሞ ዛሬ ከመመረቁ ቀደም ብሎ ለአብነትና ለዘመናዊ ትምህርት ግልጋሎት መስጠት መጀመሩ ተብራርቷል።
ትምህርት ቤቱ ከኬጂ እስከ ስምንተኛ ክፍል ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን የሚያስተምር ነው። በቀጣይም ለሁለተኛ ደረጃና ለመሰናዶ ትምህርት ቤት የሚውሉ ሕንጻዎችን በሶስትና አራት ዓመታት ገንብቶ ለማጠናቀቅ በዛሬው ዕለት የመሠረት ድንጋይ በብፁዕነታቸው ተቀምጧል።
ብፁዕነታቸው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዋ የትምህርት ሚኒስቴር ናት” በማለት የተናገሩት በደብሩ ለአብነትም ለዘመናዊ ትምህርትም ታሳቢ ተደርጎ የተሠራውን G+4 ሕንጻ በማድነቅ ነው።
ሕንጻው ለአብነት ትምህርት መዋሉ የቤተክርስቲያኒቱን ቀደም ብሎ የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት በማጠናከርና ወደፊት በማስቀጠል ዙሪያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት ባልተስፋፋበት በጥንቱ ዘመን የፊደል ገበታን ቀርጻ የአብነት ትምህርት በማስተማር የመጀመሪያዋ የትምህርት ሚኒስቴር ናት ሲሉ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ደብሩ በዘመናዊ ትምህርት ከኬጂ ጀምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ማስተማር መጀመሩ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ብቁ ዜጋን በማፍራት ዘንድ የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በተያያዘም ደብሩ 314 ካሬ የሚገመት ይዞታ በ7 ሚሊየን ብር ለመግዛት በመስማማት 3 ሚሊየን ብር መክፈሉ ተነግሯል።
በቀጣይም ደብሩ የቀረውን ክፍያ በመክፈል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ፈቃድ ካገኘ በኋላ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል G+7 ሕንጻ ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተብራርቷል።
የደብሩ አስዳዳሪ መልአከ ልዑል አማረ ታዬ፣ የደብሩ ምክትል ሊቀ መንበር ቀሲስ ኢንጂነር ሰሎሞን ወንድምአገኝና የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሊ/ብ ጥላሁን ዋለልኝ ሕንጻዎቹ ባማረ መልኩ እንዲሠሩ ላበረከቱት አመራር ከደብሩ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከብጹዕነታቸው ተረክበዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ልዑል አማረ ታዬ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ