“ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች የኅብረት ቤት ናት” በማለት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ገለጹ
ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች የኅብረት ቤት መሆኗን የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በመልእክታቸው ገለጹ።
ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች የኅብረት ቤት ናት፤ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት አንድ የሆኑ ሁሉ የሚጠመቁባት፣ የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉባት በመጨረሻም በሰላም የሚያርፉባት ናት በማለት አብራርተዋል።
ብፁዕነታቸው ይህንን መልእክት ያስተላለፉት ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ/ም በየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ስር በሚገኘው አዲስ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የደብረ ልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስንና የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርሰቲያንን በጸሎት በባረኩበት ዕለት ነው።
ደብሩ በ1998 ዓ/ም መመሥረቱን የደብሩ አሰተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ተሳፋዬ ጀንበሬ አውስተዋል።
ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ተሠርቶ ለምርቃት የመብቃቱ ምሥጢር የአከባቢው ምእመናን በንቃት የገንዘብና የማቴርያል ድጋፍ ማድረጋቸው እንደሆነ ተብራርቷል።
ከአሁን በኋላ ደብሩ ሐመረ ብርሃን ተብሎ እንዲጠራ፣ አስተዳደሪው ደግሞ መልአከ ብርሃን ተብለው እንዲጠሩ ብፁዕነታቸው ሰይመዋል።
በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት፣ መልአከ ሕይወት ቆሞሰ አባ ወልደ ኢየሱስ የሀገረ ሰብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የእቅድና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ምሕረት አምሃ መኳንንት፣ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ከፍል ኃላፊ መልአከ ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ እንዲሁም ምእመናን ተገኝተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ በመስጠት መርሐ ግብሩ ተፈፅሟል።
ዘጋቢ መ/ር ደምስ አየለ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ