መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች
የተለያዩ መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች አሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ሁሉም ሰው የጥቃት ዒላማ ውስጥ መሆኑን መረዳትና ለዚህ ሁልጊዜም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡
ለሶፍትዌሮች ወቅታዊና የዘመኑ ሶፍትዌሮችን መጫንም የኮምፒውተሮችን ደህንነት መጠበቂያ መሠረታዊ መንገድ መሆኑ ይነገራል፡፡
በተጨማሪም ቀጥተኛ የደህንነት ዝመና በየጊዜው የሚያቀርቡ እንደ ክሮም ወይም ፋየር ፎክስ ያሉ የድረ-ገጽ ማፈላለጊያዎችን መጠቀም ፣እንደ ፍላሽ፣ ሀርድ ዲስክ እና የመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎችን ሲጠቀሙ ሁልጊዜም ወቅታዊና ዘመናዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ሌላው መሠረታዊ የኮምፒውተሮችን ደህንነት መጠበቂያ መንገድ የፌሺንግ ጥቃት ሙከራዎችን ማስወገድ ሲሆን ይህም የፊሺንግ ጥቃት ብዙውን ጊዜ በኢ-ሜይል አድራሻ፣ ከዚህ በተጨማሪም በስልክ፣ በመልዕክት መለዋወጫ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች የሚፈጸም ነው፡፡
በዚህም ማናቸውም እውነተኛ የሚመስሉ የኢ-ሜይል መልዕክቶችን እና የስልክ ጥሪዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይመከራል፡፡
ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፣ የምንከፍታቸው ድረ-ገጾች እና አባሪዎች ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ መረጃ ማስቀመጫ መሣሪያዎችን በአግባቡ መያዝና ለምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች እንደውስጣዊ ደህንነት ማስጠበቂያ ሁሉ አካላዊ ጉዳት እንዳያጋጥማቸው ልንጠነቀቅ ከሚገቡ ነገሮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ጠቃሚና ምስጢራዊ ለሆኑ መረጃዎች ጥበቃ ማድረግ ማለትም እንደክሬዲት ካርድ፣ የተማሪዎች ፋይል፣ የጤና ክትትል መረጃ እና የመሳሰሉትን መረጃዎች ከስራ ቦታ፣ ከላፕቶፕ እና ሞባይል ስልኮች ላይ ማስወገድም የኮምቲውተሮችን ደህንነት መጠበቂያ አንዱ መንገድ ነው፡፡
በተጨማሪም ሞባይል ስልኮችን ደህንነት መጠበቅ የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሞባይል ስልኮችን በፍፁም ያለ የይለፍ ቃል አለመጠቀም እንደሚገባ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሌላው መሠረታዊ የኮምፒውተሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ፀረ ቫይረስ ሶፍትዌር መጠቀምና በየጊዜው መጠባበቂያ ፋይል የመያዝ ባህልን ማዳበር ሲሆን ይህም ፋይሎችን የያዙ መሣሪያዎች ላይ ጉዳት ቢያጋጥም በመጠባበቂያ የተቀመጠውን ፋይል መልሶ ለመጠቀም ያግዛል፡፡
ምንጭ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ