በመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በኩል ሲካሄድ በቆየው በ39ኛው አገር አቀፍ ስምሪት ላይ በችግሮችና በመፍትሔዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
በቀን 23/2013 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሄደው መርሐ ግብር ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ፣የሰባቱ ክፍላተ ከተሞች ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ ከየክፍለ ከተማው የተወከሉ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
በላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ” የ39ኛውን አገር አቀፍ ስምሪት በተመለከተ ችግሮችንና መፍትሔዎችን የጠቆመ ” ለውውይት የሚሆን ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ውይይት ተካሂዷል።
ከቀረቡት ችግሮች በመነሣት ከጉባኤውም አጽንኦት ተሰጥቷቸው የተጠቀሱት ችግሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦ የቤተክርስቲያን ውስጣዊ ፈተናዎች፣ የቤተክርስቲያን ውጫዊ ፈተናዎች፣ በመዋቅር መዳከም ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች፣በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተደራሽነት በኩል ያሉ ድክመቶች፣ በገጠራማው ክፍል ባሉ አብያተክርስቲያናት የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች፣ ምእመናንን በቋንቋቸው አለማስተማር፣ የቤተክርስቲያን የሀብት አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶች በሰፊው ተጠቅሰዋል።
በመቀጠልም ከቀረቡት የመፍትሔ አቅጣጫዎች በመነሣት ከጉባኤውም አጽንኦት ተሰጥቷቸው የተሰነዘሩ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል መዋቅራዊ አደረጃጀቶች ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራትና በጥናት በተደገፈ መልኩ ማዘመን፣ ውስጣዊ ችግሮችን መፍታት፣በጋራ ለቤተክርስቲያን ክብር መቆም፣ሰልጠናዎችንና ምክክርን ማስፋፋት፣ በስብሰባዎች መወሰን ብቻ ሳይሆን ተፈጻሚነት ሊኖራቸው የሚችሉ ውሳኔዎችን መወሰን፣ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ስለመፈጸማቸው ልዩ ክትትልና የአስፈጻሚ አካላት ተጠያቂነት መዘርጋት፣አሁን ያለውን አደረጃጀትና አሠራር ገምግሞና አስጠንቶ ካለው አገራዊና ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መዋቅራዊ ክለሳ ለማድረግ መሞከር፣ሕገ ቤተክርስቲያኑና ቃለ አዋዲው ለተፈጻሚነታቸው ደንብና መመሪያ ቢወጣላቸው በሕግም ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በተለያዩ ቋንቋዎች በበቂ ሁኔታ አስተርጉሞ ለምእመናን ማዳረስና በቋንቋቸው ማስተማር፣ ሒሳብ የሚሠራባቸውን ደረሰኞችንም ጭምር በተለያዩ ቋንቋዎች አሳትሞ በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባና ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ አካል ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ተነግሯል።
በተያያዘም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም በመጪው ርክበ ካህናት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ እነዚህን ጉዳዮች አንሥቶ እንደሚወያይ ይጠበቃል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባን ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ መመራቱን ተከትሎ ያካሄደውን አንደኛ መደበኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በተመለከተና አጠቃላይ በአሁን ጊዜ እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎች ለጉባኤው አብራርተዋል።
በመጨረሻም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ መመሪያዎችን አስተላልፈው ጉባኤው በጸሎት ተጠናቋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ