የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የምስጋና ምስክር ወረቀት አበረከተ
የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር በአሁኑ ሰዓት 450 ሴቶችንና 650 ሕጻናትን የሚንከባከብና የሚያስተምር የበጎ አድራጎት ማኅበር ነው።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ይህንን በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ፊት መልካም የሆነውን የማኅበሩን ሥራ ለማበረታታትና የድርሻውን ለመወጣት በሀገረ ስብከቱ ምግባረ ሰናይ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተሰበሰቡ የትምህርት ቁሳቁሶችንና የተለያዩ አልባሳትን ከአንድም ሁለት ጊዜ ለማኅበሩ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበርም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ላደረገው አስተዋጽኦ የምስጋና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል።
የምስጋና ምስክር ወረቀት ስጦታው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የሀገረ ስብከቱ ምግባረ ሰናይ ዋና ክፍል ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ በተገኙበት በማኅበሩ ተወካዮች በኩል ለሀገረ ስብከቱ ተበርክቷል።
የማኅበሩ ተወካዮች ለብፁዕነታቸው፣ ለዋና ሥራ አስኪያጁና ለ ምግባረ ሰናይ ዋና ክፍል ኃላፊው ማኅበሩ ያለበት ቦታ ድረስ በመገኘት ጉብኝት እንዲያደርጉና ድጋፉም ለወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ማኅበሩ እየሠራ ያለውን መልካም ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ