የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የማይተካ ሚና እንዳለው በ39ኛው የሰበካ ጉባኤ ስልጠና ላይ ተገለጸ!!
መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ፡የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሃይማኖት ጸጋዬ ገ/ዮሐንስ፡ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኙ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፡ ጸሐፊዎች እና የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አስተባባሪነት የ39ኛውን መደበኛ ሰበካ ጉባኤ የስምሪት ሪፖርት አስመልክቶ በቀረበው ዳሰሳዊ ጥናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ብ ሳሙኤል ደምሴ በዚህ በያዝነው ዓመት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚደረገውን አንደኛ መደበኛ ሰበካ ጉባኤ በወርኃ የካቲት ማደረጉን አስታውሰዋል፡ የስልጠና እና የምክክር መርሐ ግብሩ የተዘጋጀው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል የጋራ ትብብር ሆኖ በክፍለ ከተማው አስተባባሪነት መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡
የመ/ፓ/ጠ/ቤተ ክህነት የ39ኛው አጠቃላይ መደበኛ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደረጉን ተከትሎ ችግር ካለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ውጭ በመላው አህጉረ ስብከት አጠቃላይ ስምሪት መደረጉን እና ሪፖርት መቅረቡን ገልጸዋል፡ከሁሉም የስምሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማደራጃ መምሪያው የቀረበው ሪፖርት የቤተ ክርስቲያናችንን አሁናዊ ሁኔታ በግልፅ ያሳየ መሆኑን የጠ/ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊው ላዕከ ሰላም ሰሎሞን ቶልቻ አብራርተዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ጠዋትና ከስአት ለአንድ ቀን ያክል የተደረገ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ሀገረ መንግሥትን ከመገንባት አንጻር ያላት ሚና፡በቤተ ክርስቲያናችን እየተፈጸመ ስላለው የክህነት አገልግሎትና የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀትና ጉዞው እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሚሉ አራት የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ዳሰሳዊ ጥናቶች ቀርበዋል፡ውይይትና ምክክርም ተደርጎባቸዋል፡፡
ይኸው የ39ኛው አጠቃላይ መደበኛ የሰበካ ጉባኤ የስምሪት ስልጠና እና ምክክር በቀሩት ስድስት ክፍላተ ከተሞች ላይ የሚቀጥል መሆኑንም ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ