ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና መ/ር አካለወልድ ተሰማ በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ትምህርተ ወንጌልና የሥራ መመሪያ ሰጡ

የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ትምህርተ ወንጌልና የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በቦታው ክቡር አባ ወልደኢየሱስ ሰይፈ የሀገረ ሰብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፥ ክብር መልአከ ሣህል ቆሞስ አባ ተክለ ብርሃን ደስታ የደብሩ አስተዳዳሪ፥ የደብሩ ካህናት አገልጋዮችና በርከት ያሉ ምእመናን ተገኝተዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ ክብር መልአከ ሣህል ቆሞስ አባ ተክለ ብርሃን ደስታ የቤተ መቅደሱ አገልግሎት እንደ ደብረ ሊባኖስ በ7 ካህናት የሚቀደስና በዕለተ ሰንበት በሁለት መንበር በ14 ቀዳሲያን እንደሚቀደስ አብራርተዋል።
ዕለቱን የተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር አካለወልድ ተስማ ተሰጥቷል።
ትምህርቱ 3ኛ ሳምንት የኢየሱስ ፆም ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብቶ ቃለ ሃይማኖትን በማስተማር ቤተ መቅደሱን ከወንበዴዎች ያፀዳበት ዕለት መሆኑን በመጥቀስ ዛሬም ምዕመናን ሰውነት ቤተ መቅደሳችንን ከኃጢያት በማንጻት ቃሉ በሚፈቅደው መሠረት በንጽህና መኖር አለብን ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም “የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል” በሚል ከቅዱስ ዳዊት መዝሙር መነሻ በማደረግ የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የመላእክት ተራዳኢነትና ጥበቃ የሚያትት ሰፋ ያለ ትምህርትና አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የደብሩ የጸበል ቦታ ጎብኝተዋል።


ዘጋቢ መ/ር ደምስ አየለ
ፎቶ በመ/ር ወሲሁን ተሾመ