የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ራሱን ችሎ በራሱ ሊቀ ጳጳስ መመራት ከጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አካሄደ
የጥቅምት 2013 ዓ/ም ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ በራሱ ሊቀ ጳጳስ አንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ ሀ/ስብከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።
የሀገረ ስብከቱ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እየተካሄደ ያለው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሲሆን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ የበላይ ኃላፊና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየክፍሉ ዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበበ ሀ/ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርት እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጀምሯል።
በመቀጠልም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለጉባኤተኛው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው “ወበኲሉ ታደልው ሎቱ በኲሉ ምግባረ ሠናይ እንዘ ትፈርዩ ወትሰምሩ በአእምሮ እግዚአብሔር በበጎ ሥራ ኹሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ……ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን (ቆላ. 1.10-11) በሚል መነሻነት የበጎ ሥራ ውጤት በዓይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ፣ እግዚአብሔርና ሰዎችን የሚያስደስት፣ በጥበበ እግዚአብሔር የሚያሳድግና በእምነት የሚያንጽ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ጌታችን መድኃኒታችን “ከማሁ ይብራህ ብርሃንክሙ በቅድመ ሰብእ ከመይርአዩ ምግባሪክሙ ሠናየ ወይሴብሕዎ ለአቡክሙ ዘበሰማያት” መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለው አባታችሁን ያከብሩ ዘንድ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ (ማቴ.5.16) ባለው መሠረት የመልካም ሥራ ፍሬ ውጤት ሌሎችን የሚያስተምር የራቁትን የሚያቀርብ ሲሆን እግዚአብሔር አባታችንና አምላካችንም በምድር ሆነን በምንሠራው በጎ ሥራ እንደሚከብር አስገንዝበዋል።
በዘመናችን በቤተክርስቲያን አገልግሎት ብዙ ፍሬ ከምናፈራባቸው ምግባራት መካከል አንዱ የሰበካ ጉባኤ በመሆኑ አባቶቻችን በመሠረቱት መሠረት ካህናትና ምዕመናን እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ሕብረት ተዋቅሮ እየተሠራበት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር አያይዘውም ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሌሎች አህጉረ ስብከቶች ሲካሄድ የነበረ ሲሆን በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ከዚህ በፊት ተካሂዶ እንደማያውቅ በመግለጽ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደዚህ ታላቅና ከባድ የቅድስት ቤተክርስቲያን ኃላፊነት ከመጣን በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እገዛና የብፁዓን አባቶች ፀሎት ረድቶን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለውን የመልካም የአስተዳደር እጦት ዋነኛ ቁልፍ ምክንያት የሆነውን ቅጥርን፣ ዝውውርን፣ ዕድገትንና የተንዛዛ ቢሮክራሲ የመሳሰሉትን ለሙስና በር ከፋች የሆኑትን ዋነኛ ተግባራት እንዲቆሙ በመሥራት ላይ ነን ብለዋል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ለሙስና በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት ሀ/ስብከቱ ዘመኑ የሚጠይቀውን በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ “የሰው ሐብት አስተዳደር መረጃ ሲስተም /Human Resource Management System/፣ የንብረትና ሐብት መረጃ /Asset Management System/፣ የመዝገብ ቤት መረጃ /Archive Management System/፣ የአላቂ ንብረት መረጃ /Stoke Management System/ የሚባሉት ሲስተሞች/ሥርዓቶች በመዘርጋት በትግበራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሥራዎቻችን እንዲሳኩና፣ ችግሮች እንዲወገዱ፣ ለማድረግ ዋናው በዕቅድ መመራትና በጎ ሥራ ሁነኛ መንገድ መሆኑን በመጥቀስ በቃለ አዋዲው መመሪያ መሠረት ሰበካ ጉባኤው የተዋቀረው ልማት በማስፋፋት የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር፣ ምእመና እምነታቸውን ጠብቀው የመንግሥተ እግዚአብሔር ወራሾች እንደሆኑ ወጣቶች ፍቅረ ቤተ ክርስቲያን ተላብሰው የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆኑ፣ በትምህርተ ሃይማኖት በግብረ ገብነት ተኮትኩተው እንዲያድጉ ለማድረግ ነው ካሉ በኋላ “አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በትንሹ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ እንዳለው” ማቴ. 25፡21 በየአጥቢያው በሰበካ ጉባኤ የተመረጡ አባላት ለስብከተ ወንጌል እና የሰንበት ት/ ቤት ልዩ ትኩረት በመስጠት ኦርቶዶክሳዊው ትውልድ በመንፈሳዊነት እንዲታነፅ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የሰበካ ጉባኤ አባላት የተሰጠን ሐብትና ፀጋ አውቀን ጥሪያችን አክብረን እንደባለ 5ቱ መክሊት ትንሹን አብዝተን ሰማያዊ ዋጋ የሚያሰጠውን በጎ ሥራ በመሥራት ከአባቶች የተረከብነውን ሰበካ ጉባኤ ቅድስትቤተ ክርስቲያን በልማት አሳድገን፣ መልካም አስተዳደር አስፍነን እኛም ለቀጣዩ ትውልድ እንድናሸጋግር ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ይርዳን ብለዋል።
በመቀጠልም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመ/ር አካለ ወልድ ተሰማ የሀገረ ስብከቱን ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ቀርቧል። በሪፖርቱ ሀገረ ስብከቱ በ2005 ዓ/ም በቀዋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ በ7ቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዋቅሮ በአሁን ሰዓት በሥሩ 246 ገዳማትና አድባራት የሚያስተዳድር መሆኑን በመግለጽ በሀገረ ስብከቱ በየክፍሉ የተከናወኑ የዓመቱ ስኬታማ ክንውኖችና የነበሩትን ተግዳሮቶች ተደምጧል።
በሀ/ስብከቱ የሒሳብ ዋና ክፍል የዐመቱ ጠቅላላ ገቢ ብር 327,173,307.56 ሲሆን የዓመቱ ልዩነት በዕድገት ብር 40,909,498.10 መሆኑን ተገልጿል።
በመጨረሻም የ7ቱ ክፍለ ከተሞች ራፖርት ቀርቧል። ከሰዓት በፊት የነበረ መርሐ ግብሩም በዚህ ተጠናቋል።
ከሰዓት በኋላ የነበረ መርሐ ግብርም “ሰበካ ጉባኤ ትናንትና እና ዛሬ” በሚል ርእስ ዳሰሳዊ የጥናት ጽሑፍ በመ/ር ሰሎሞን ቶርቻ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ የቀረበ ሲሆን በቀረበው ዳሰሳዊ የጥናት ጽሑፉ፡ ቅድመ ሰበካ ጉባኤና ድኅረ ሰበካ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ዓለም የሚያደንቀው የሰበካ መንፈሳዊ አደረጃጀት ፣ ሰለ ሰበካ ጉባኤ የግንዛቤ መፍጠርና ማሳደግ ሥራ፣ የቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ የመረጃ አያያዝ ጠቀሜታና የስታስቲክ ዋና ጠቀሜታ ለቤተ ክርስቲያን የሚሉ ዋና ዋና ነጥቦች ይገኙበታል።
በመጨረሻም በዕለቱ በቀረበው ዳሰሳዊ የጥናት ጽሑፍና ሪፖርት መሠረት ያደረገ የውይይት መርሐ-ግብር ተካሂዷል። በውይይቱ ከጉባኤተኞች የተለያዩ ሐሳቦች የተነሱ ሲሆኑ በጥናቱ አቅራቢ፣ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። የዕለቱ መርሐ-ግብርም በዚህ ተጠናቋል።
መርሐ- ግብሩ ነገም እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን እኛም መርሐ ግብሩ እየተከታተልን ወደ እናንተ የምናደርስ መሆናችንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።
ፎቶ፡ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ