ምንዱባንን መደገፍ እና ያዘኑትን ማጽናናት የቤተ ክርስቲያን ዋና ተግባር ሊሆን ይገባል…..ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፡የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፡ የአዲስአበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እና የኒውዮርክ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እንዲሁም የዕርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መግለጫ ተሰጥቷል፡።ይገኛል ተብሎ ከታቀደው 81 ሚሊዮን ብር ውስጥ 35 ሚሊዮን 940 ሺህ ብር የፋይናንስ ድጋፍ መገኘቱንም ኮሚቴው አሳውቋል፡፡
በመግለጫው ላይ እንደተደመጠው ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይና በቤንሻንጉል ክልሎች በተፈጠረው ወቅታዊ ክስተት የተነሣ ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች ዕርዳታ እንዲሰባሰብና ለችግሮች እንዲሰጥ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አስቸኳይ መልስ በመስጠትና ለተፈናቀሉ ወገኖቹም ያለውን ሰብአዊ አጋርነት ለማረጋገጥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት 15 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ባደረጉት ንግግር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከቅዱስ ወንጌሉ አገልግሎት ጎን ለጎን ምንዱባንን መደገፍ እና ያዘኑትን ማጽናናት ዋና ተግባሯ አድርጋ መቀጠል ይገባታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም በሀገረ ስብከታችን እንደዚህ ዓይነት የምግባረ ሠናይ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥል፡ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤት እያላቸው ቤት አልባ ለሆኑ፡ ሰላምን ፈልገው ሰላምና ጤናን ላጡ በጸሎት ከማሰብና ከማበረታታት ጀምሮ ልቡ የፈቀደውንና የቻለውን ሁሉ ይረዳ ዘንድ መንፈሳዊ ግዴታ አለበትና ወገኖቻችንን እናግዝ ሲሉ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
በሌላ ዜና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብቸኛ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሆነው የቅድስት ልደታ ለማርያም የጤና ሳይንስና ቢዝነስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብቸኛ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሆነው የቅድስት ልደታ ለማርያም የጤና ሳይንስና ቢዝነስ ኮሌጅ የተማሪዎች ምርቃት የካቲት 6/06/2013 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት “ጽርሐ ተዋሕዶ ” አዳራሽ ተካሂዷል።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱላይ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ፣የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራአስከያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች እና ተመራቂዎች ተማሪዎች በተገኙበት ምረቃቱ ተካሄዷል።
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፦ ከEOTC TV ፌስቡክ ገጽ