በቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በምዕራፈ ሰማዕታት ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን የዝክረ ሰማዕታቱ መታሰቢያ በዓል ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት ታስቦ ዋለ
ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሃያ አራት ቀበሌ እየተባለበሚጠራው
አካባቢ በምዕራፈ ሰማዕታት ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱና የቦሌ ክፍለ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የደብሩ ካህናትና የተጎጅ ቤተሰቦች በተገኙበት የአንደኛ ዓመት ዝክረሰማዕታት በዓል ተከብሮ ውሏል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በሥጋ የተለዩ ምዕመናኗን በምታስብበት ሥርዓተጸሎተ ማለትም በጸሎተ
ፍትሐት፡በቅዳሴና በትምህርተ ወንጌል ታስቦ የተከበረውን የዝክረ ሰማዕታት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ እና በክፍለከተማው ቤተክህነት እንዲሁም በአካባቢው ወጣቶች አስተባባሪነት እንደሆነ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ ዛሬ የተገናኘንበት ዓላማ የሁለት ወንድሞቻችን በሥጋ መለየትና የሌሎች ኦርቶዶክሳውያንን አካል መጉደል እያሰብን ልናለቅስ አይደለም፡ ይልቁንም ክርስትናን በተግባር ያስተማሩና በቀደሙት ሰማዕታት መንፈሳዊ ኅብረት የተደመሩ ወገኖችን ለመዘከር ነው፡ ስለሆነም የእነዚህ ሰማዕታት ወላጆች፡ የቅርብ ጓደኞች እንዲሁም ዘመድና ወዳጆች ሁሉ ጥቁር ልብስ ለብሳችሁ ሳይሆን ነጭ ለብሳችሁ፡አዝናችሁ ሳይሆን ደስ ብሏችሁ የወገኖቻችንን መታሰቢያ አክብሩ በማለት አሳስበዋል፡፡
በዕለቱ የተገኙት የአካባቢው ወጣቶች የተጎጅ ቤተሰብን የተመለከተ የካሳ ክፍያ፡ በደብሩ ለሚያገለግሉ አገልጋይ ካህናት የሕጋዊነት የቅጥር ደብዳቤ እና የደብሩን ባለይዞታነት የሚያረጋግጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአሁን በፊት በነበረው የጋራ ውይይት በፍጥነት እንደሚፈጸሙ ቃል የተገቡ የሥራ ክንውኖች መሆናቸውን አሳታውሰው አሁንም ጊዜ ሳይሰጣቸው መልስ እንዲያገኙና ችግሮቹ እንዲፈቱ ሲሉ ለብፁዕታቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ይህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተውና ለዚህ አገልግሎት የበቃው የዛሬ ዓመት ሰማዕትነት በተቀበሉትና አካላቸውን ባጎደሉት ልጆቻችንና የእምነት አርበኞቻችን ተጋድሎ ነው፡ እኛም የልጆቻችን ተጋድሎ ለመዘከርና ዕለቱን ለማሰብበዚህ ተገኝተናል፡ ሥርዓተ ጸሎተም አድርሰናል ብለዋል ዕለቱን በማሰብ ያስተባበሩትን አመስግነዋል፡፡
አያይዘውም በወጣት ልጆቻችን የተጠየቁትን ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በቀጥታ መልስ መስጠት
የምንችለውን በመመለስ፡ ከመንግሥት ጋር መነጋገርና መጻጻፍ ያለብንን ጉዳይ ደግሞ በመነጋገር በየደረጃው እንመልሳለን፡ እናንተ ግን የነበራችሁን መንፈሳዊነታችሁ ጨምራችሁ እና በርትታችሁ ክርስቲያናዊ ጉዟችሁን ቀጥሉ በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም ወር ጥር ላይ በመንግሥት የጸጥታ አካላትና በአካባቢው ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናን መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተነሣ በአሳዛኝ ሁኔታ የሁለት ወንድሞች ሕይወት ማለፍና በተወሰኑ ወጣቶች የአካል ጉዳት መድረሱ ብዙኃንን ያሳዘነ ድርጊት መሆኑ የሚታወስ የቅርብ ድርጊት ነው፡፡
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡-መ/ር ዋሲሁን ተሾመ