የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
ብፁዕነታቸው “በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው” እንደገለጹት የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ስናከብር “እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6፥4-5) የሚለውን መለኮታዊና ሕያው የሆነውን ቃል በውስጣችን በማሰብ ማክበር እንደሚገባን መልእክት አስተላልፈዋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በ30 ዓመቱ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የመጠመቁ ዓላማ ምሥጢረ ሥላሴን ለመግለጥ (ማቴ 3፤16-17)፣ ጽድቅን ሁሉ ሊፈጽም (ማቴ 3፡15)፣ ትሕትናን ሊያስተምረን (ማቴ 3፡13-15)፣አርአያ ሊሆነን እንደሆነ ትኩረት በመስጠትና ከልብ በማስታወስ በዓሉን ማክበር እንደሚኖርብን የበዓሉን ጭብጥ መልእክት በመግለጽ አብራርተዋል።
አያይዘውም በዓሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ በመሄድና በእርሱ እጅ በመጠመቅ ትህትናን በተግባር ፈጽሞ ያሳየበትና ያስተማረበት ዕለት እንደመሆኑ መጠን እኛም የክርስቶስን ፈለግ በመከተል የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ወላጅ አልባ ሕጻናትን በመጎብኘትና በመንከባከብ፣በኃዘን ላይ ያሉትን በማጽናናትና ትህትናን አብዝተን በተግባር በመፈጸም በዓሉን ማክበር እንደሚገባንም መክረዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በዓሉ የሰላም፣የጤና፣ የአንድነትና የፍቅር እንዲሆንልን ከምንም በላይ የበዓሉ መንፈሳዊ ይዘት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን ለአባቶችና ለመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካላት ትዕዛዝና መመሪያ በመታዘዝ፣ በስሜት ሳይሆን በማስተዋልና በእምነት፣ እርስ በእርስ በመደማመጥና በመናበብ፣ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን በመጠበቅና የጤና ሚንስተር መመሪያዎችን በመተግበር ማክበር እንደሚኖርብን አጽንዖት ሰጥተው አባታዊ መመሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ