የአዲስ የአበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብሥራት ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ
ታህሳስ 22 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ አህገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ነጋሽ፡ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/ም ዘካርያስ ዐዲስ ፡የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን አስተዳደሪ መልአከ አሚን ለይኩን አበጀ፡ የደብሩ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሥርዓት አበበ አለማየሁ ፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የበርካታ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፡ የደብሩ ማኅበረ ካህናት እና የደብሩ የሰ/ት/ቤት መዘምራን ወጣቶች እንዲሁም እጅግ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በተለምዶ ሳር ቤት በሚባለው አካባቢ በሚገኘው ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሰረበትን ዕለት የሚዘክር በዓለ ንግሥ በዝማሬ እና ትምህርት ወንጌል ታጅቦ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል::
መርሐ ግብሩን የመሩት የደብሩ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሥርዓት አበበ አለማየሁ “የዛሬዋ ዕለት የሕይወታችን መድኅን የሆነውን ክርስቶስን ያገኘንባት ቅድስት ድንግል ማርያም ፡ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብሥራት ቃል የሰማችበት ዕለት ነውና እንኳን አደረሳችሁ፡በአሁኑ ስአት መንፈሳዊ አገልግሎቱን በመምራት ላይ የሚገኙት የደብራችን አስተዳዳሪ የደብሩን ሁለንተናዊ ዕድገት ከማሳለጥ እና ከማፋጠን ጀምሮ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ከፊት ሆነው በመምራት ወደር የማይገኝላቸው አባት ናቸው፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ሊቃውንት አንዱ መሆናቸውን አስመስክረዋልና በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ገልጸዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ለይኩን አበጀ “ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ እንኳን ወደ ጥንታዊው ደብራችን በሰላም መጡልን: የእኛ ደብር ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን እጅግ ዕድለኞች ናችሁ፡ ምክንያቱም ከብፁዕ አባታችን ለሦስተኛ ጊዜ አባታዊ ቡራኬ ለመቀበል ዕድል አግኝተናልና ነው ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመጻሕፍት መምህር መጋቤ ሐዲስ አባ ኒቆዲሞስ “እግዝእትነ ማርያም ነበረት በኅሊና አምላክ” በሚል ርእስ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብሥራት ቃልና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገረ ፅንሰት እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን ግብር እና የቅድስት ድንግል ማርያምን የትህትና ምሳሌነት ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” ዕለቱን አስመልክቶ የተማርነው ትምህርት በቂ ነው፡ ይህንኑ ትምህርት ወደ ተግባር እንለውጠውና ሕይወታችንን እንምራበት፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው በተማርነው ልክና መጠን እንድንኖር ነው፡ መንፈሳዊነታችን ይጨምር ለመንፈስ ቅዱስ አሠራርም ምቹ እንሁን በማለት አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም እኔ ወደዚህ ቦታ በተደጋጋሚ የመጣሁት በዚህ ደብር የምታገለግሉት ካህናትና የምትገለገሉት ምዕመናን በሌላ ቦታ ካሉት ልጆቼ በልጣችሁብኝ አይደለም ይልቁንም ከአንድ ዓመት በፊት በደብሩ ዙሪያ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች እንደነበሩና የጥንት ታሪኩ እንደኮሰሰ የደብሩ አስተዳዳሪ አጫውተውኝ እንድፀልይም አሳስበውኝ ነበር፡ እኔም ይህ በርካታ ሊቃውንት የወጡበትን እና ከቀደምት የወንጌል መናገሻ ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው ብሥራተ ገብርኤል እንደዚህ ታሪኩ ኮስሶ በመስማቴ አዝኜ ስለቦታው ክብር ስጸልይ ነበር፡ ዘንድሮ ደግሞ ያ ሁሉ ተለውጦ የሰላምና የወንጌል ልማቱ ተፋጥኖ ስላየሁት ለውጡን ለመመልከት መጥቻለሁ፡ የአንድ አስተዳዳሪ ዋና ሥራም ቅዱስ ወንጌሉን ማስፋፋትና ሰላምን ማስፈን ነው ፡የሕንጻ ግንባታው ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣ የመሬት ላይ ልማት ነው፡ በዚህ ቦታ ሁሉም በየደረጃው እየተሠራበት በማየቴ ደስተኛ ነኝ፡ መንፈሳዊነት ሳይጠፋ፡ እምነት ሳይጓደል፡ ቅዱስ ወንጌሉም ሳይኮስስ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንችላለን፡ ይህንን ማሳካት ከቻልን እግዚአብሔርን ደስ ማስኘት ይቻላልና ወደፊትም በዚሁ የቀና መስመር በመጓዝ የደብሩን ታሪካዊ ክብር አስጠብቁ በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ይጎብኙ
www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
ዩትዩብ ቻናል:- www.youtube.com/channel/UCtYqL7fu87AVTGHaZDPToFg