ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጸ/ቤት ሠራተኞችና በክፍለ ከተማው ሥር ከሚገኙት የአድባራትና የገዳማት አገልጋዮች ጋር ትውውቅ አደረጉ

ዛሬ ታህሳስ 14/2013 ዓ/ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በየካ ደበረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ከየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሠራተኞች እና በክፍለ ከተማው ሥር ከሚገኙት የ46 ገዳማትና አድባራት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፥ ምክትል ሊቃነ መናብርት፥ ጸሓፊዎች፥ ስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር አድርገዋል።

በቦታው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ክፍል ኃላፊዎች፦ ዋና ጸሐፊው መ/ር ታዴዎስ ሽፈራው ፥ የካህናት አስተዳደሩ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ እና የህዝብ ግንኙነቱ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ፡ በክፍለ ከተማው ከሐምሌ እስከ ታህሳስ የተከናወኑትን ሥራዎች አጭር ሪፖርት በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍስሕት ግርማ ቀርቧል፤ አያይዘውም የዓመቱ ዕቅዳቸውን አሰምተዋል።

ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች የተወከሉ የተወሰኑ ሰዎች ለብፁዕነታቸው የእንኳን ደህና መጡልን መልእክታቸውንና ደስታቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ በነበሩበት ጊዜ የጀመሩትን ሥራዎችና ዕቅዶች እንዲያስቀጥሉልን እንወዳለን፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት በጠበቀ መልኩ በሀገረ ስብከቱ ሁነኛ ለውጥ እንዲመጣልን እንፈልጋለን ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ስለ ተዘጋጀው የትውውቅ መርሃ ግብር አመስግነው ከዚህ በፊት በሀገረ ስብከቱ በነበርኩበት ጊዜ በእንዲህ መልኩ የትውውቅ መርሃ ግብር እንዳናደርግ ዕድሉም፣ ልምዱም አልነበረም፤ አሁን ግን በምታዘጋጁት መርሃ ግብር እናንተ ወደ እኛ ሳትደክሙ እኛ ወደያላችሁበት እየመጣን እየተዋወቅን ነው በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።

ለውጡን በተመለከተ ለተነሣ ጥያቄ ሲመልሱ፦ በቤተ ክርስቲያን ቅጽበታዊ የህንጻም ሆነ የቁስ ለውጥ እንዲመጣ አንጠብቅ፤ ሂደታዊ ለውጥ ነው የሚኖረን፤ በመጀመርያ የአእምሮ፥ የህሊና እና ዘመኑን የዋጀ የአሠራር ለውጥ እንድናመጣ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ልባዊ የአሠራር ለውጥ ሊኖረን ይገባል። ሁላችንም ከቤተ ክርስቲያን የተረከብነውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በመቀጠልም ሀገረ ስብከት፥ ክፍለ ከተማና አጥቢያዎች በመቀናጀት ሁላችን የለውጡ አካላት ሆነን በመነሣት ለሥራችን እንቅፋት የሚሆኑ አሠራሮችን አስወግደን ሥራችን ሁሉ በመሪ ዕቅድና በአግባቡ እንዲሁም የሥራ ሰንሰለቱን ጠብቀን ከሄድን ለውጡ ይመጣል፤ ሙስናም ሆነ ሌሎች በቤቱ ያሉ ብልሹ አሠራሮችም በዚህ መልኩ ማስወገድና ማስቀረት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ተቀዳሚ ሥራዋ አድርጋ መሄድ እንዳለባትና ለስብከተ ወንጌል አስፈላጊ የተባለውን ሁሉ ማሟላት እንዳለባት አብራርተዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለጉባኤው አባታዊ ምክርና መመሪያን በማስተላለፍ መርሃ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል።

መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ: በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ