የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት አሠራሩን ለማዘመን ከማኑዋል ሲስተም ወደ ኮምፒውተራይዝድ ሲስተም የሚያደርገውን ጉዞ አጠናክሮ ለመቀጠል ለሚመለከታቸው አካላት ስለመረጃ አሰባሰብና አሞላል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጠ
በዛሬው ዕለት ታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የሀገረ ስብከቱ የየክፍሉ ኃላፊዎች፣የሰባቱ ክፍላተ ከተሞች የሰው ኃይል አስተዳደሮች፣የገዳማትና አድባራት ጸሐፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ስለ መረጃ አሰባሰብና አሞላል የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል።
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከአሁን በፊት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ሀገረ ስብከቱን በመሩበት ወቅት ተጀምረው የነበሩትን ቴክኖሎጅ ተኮር ሥራዎችን ማለትም:-
- የሰው ሀብት አስተዳደር ሲስተም (Human Resource management system)
- የንብረትና ሀብት አስተዳደር ሲስተም (Asset Management System)
- የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደር ሲስተም (Archive File Management system) እና
- እስቶክ አስተዳደር ሲስተም (Stock Management System) የመሳሰሉትን ዘመናዊ የአሠራር መተግበርያ ሲስተም ሥራ ላይ እንዲውሉ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ብጹዕነታቸው በሙሉ ኃላፊነት ሀገረ ስብከቱን ለመምራት ከተረከቡበት ዕለት ጀምሮ ለዚህ ዘመናዊ አሠራር ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ በሀገረ ስብከቱ የአይቲና ዶክመንቴሽን ክፍል ኃላፊ በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እስከ አድባራትና ገዳማት ድረስ በመውረድ መረጃ በፍጥነት እንዲሰበሰብ መምሪያ ሰጥተው፤ የተዋቀረውም ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በመተግበር ላይ ይገኛል።
ሆኖም ግን ኮሚቴው በፍጥነት ሥራውን እንዳያከናውን በክፍለ ከተሞች ሠራተኞች፣በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ዘንድ ስለ አሠራሩ ያለው የግንዛቤ እጥረት እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል።
ከዚህ በፊት በሀገረ ስብከቱ የአይቲና ዶክመንቴሽን ክፍል ኃላፊ በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ የግንዛቤ መግለጫ የተሰጠ ቢሆንም አሁን ድረስ ስለ አሠራሩ በሠራተኞች ዘንድ ብዥታ በመኖሩ ምክንያት በድጋሜ ገለጻ እንዲሰጥ ኮሚቴው መወሰኑ ተነግሯል።
ብፁዕነታቸው የኮሚቴውን እንቅስቃሴና ውሳኔ አድንቀው ስለ አራቱ ሲስተም አጠቃላይ ፋይዳ ና ጠቀሜታ በዝርዝር አብራርተው የገለጹ ሲሆን ቤተክርስቲያናችን ከዘመኑ ጋር እንድትጓዝ ፣አሠራራችን ቀልጣፋ እንዲሆን፣ያለንን የሰው ኃይል በቀላሉ እንድናውቅ፣በየአብያተክርስቲያኑ የተመጣጠነ የሰው ኃይል እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፤አያይዘውም በአጭር ጊዜ ውስጥ በኃላፊነትና በትጋት ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ አባታዊ መመሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የዛሬውን የግንዛቤ መግለጫ የሰጡት የኮሚቴው አባል የሆኑት መ/ር ሽፈራው እንደሻው ሲሆኑ በገለጻቸውም ላይ የሰው ሀብት አስተዳደር ሲስተም፣ የንብረትና ሀብት አስተዳደር ሲስተም፣የመዝገብ ቤት ፋይል አስተዳደር ሲስተም እና የእስቶክ አስተዳደር ሲስተምን ያካተቱ ሲሆን ወደ አድባራትና ገዳማት የተላከውንም ባለ ሁለት ቅፅ አክለው ሰፋ ባለ መልኩ ስለ መረጃ አሰባሰብ እና አሞላል አብራርተውና ተንትነው ገልጸዋል።ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአግባቡ መረጃ መሰብሰብና መሙላት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፍትሀዊ የሥራ ክፍፍል እንዲኖር፣ ቀልጣፋ መረጃ ለመስጠጥ፣ የሥራ ዋስትና እንዲኖር፣አሥራሩን ለማዘመን፣ መመሪያዎችን በፍጥነት ለማስተላለፍ እንደሚጠቅም አብራርተዋል።
በመጨረሻም ከመድረኩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ቀርበዋል።ለተነሡት ጥያቄዎች በሀገረ ስብከቱ የአይቲና ዶክመንቴሽን ክፍል ኃላፊው መ/ር ዘሩ ብርሃኔና የግንዛቤ ማስጨበጫውን በሰጡት በመ/ር ሽፈራው እንደሻው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ