ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን የጥምቀተ ባሕር ማክበሪያ ስፍራ የሆነውን ጃንሜዳ ጎበኙ

ዛሬ ታህሳስ 11/2013 ዓ/ም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ወጣቶች እና በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እየጸዳ የሚገኘውን የጥምቀተ ባሕር ማክበሪያ ስፍራ ጃንሜዳን ጎብኝተው ባርከዋል።

በቦታው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ፥ በርከት ያሉ ምእመናን እና ስፍራውን ሊያጸዱ የመጡ ወጣቶችን ተገኝተዋል።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ባለፈው ጊዜያት በዚህ አከባቢ ስናልፍ ለጥምቀተ ባሕር ማክበሪያ የተቀደሰ ስፍራ የገበያ ማእከል ሆኖ ስናይ እያዘን እናልፍ ነበር፤ አሁን ግን ቦታው እየጸዳ በዝግጅት ላይ መሆኑን ስናይ ደስ ብሎናል እናንተም እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። ኣያይዘውም ሀገረ ስብከቱ ቦታው ሕጋዊ ካርታ እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም “መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤” (ሮሜ13:3) በሚል ኃይለ ቃል መነሻነት ስፍራውን ለማጽዳት በቦታው ለተገኙት ወጣቶችን በቤተ ክርስቲያን ስም አመስግነዋል። በማስከተልም ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋቸውን ላቅ ያለ መሆኑን በመግለጽ ወጣቶቹ መልካም የሆነ ሥራቸውን በይበልጥ እንዲቀጥሉበት አበረታትተዋል።

በመቀጠልም ጃንሜዳን ጨምሮ ስለ ሌሎችን የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ሕጋዊ የይዞታ ካርታ እንዲኖራቸው ሀገረ ስብከቱ በንቃት እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ባለ መሰልቸትና መታከት እስከ መጨረሻ በንቃት እንደሚሠሩ አብራርተዋል። ምእመኑም የይዞታው ካርታ እንዲሳካ በሚችለው ሁሉ እና በጸሎት ከሀገረ ስብከቱ ጎን እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም ወጣቱ መልካም የሆነውን ሁሉ፥ ለቤተክርስቲያን ብሎም ለሃገር የሚበጀውን ሁሉ ዘወትር ባለ መሰልቸትና መታከት እንዲሠራ በማሳሰብ ዝግጅቱን በጸሎት ዘግተዋል።

መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ