የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከትሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ያሬድ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ
ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ አህገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ-ክርስቲያን አስተዳደሪ መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የበርካታ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የደብሩ ማኅበረ ካህናት እና የደብሩ የሰ/ት/ቤት መዘምራን ወጣቶች እንዲሁም እጅግ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ጎተራ አካባቢ በሚገኘው ደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማ የተቀበለበትን ዕለት የሚዘክር በዓለ ንግሥ በዝማሬ እና ትምህርት-ወንጌል ታጅቦ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል::
መርሐ ግብሩን የመሩት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ተስፋ ማርያም ነጋሽ በዛሬው ዕለት የምናከብረው ክብረ በዓል ታላቁ የቤተ ክርስቲያን የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የብዙ ጊዜ የሕይወት ውጣ ውረዱን በትእግስት ካለፈ በኋላ በመንፈስ ወደ ሰማይ ተነጥቆ የመላእክትን ዝማሬ የሰማበት እና “ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” በማለት ለምድራችን ያስተጋባበት ዕለት ለመዘከር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አይይዘውም ይህንን ታላቅ የዜማ ባለቤትና የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ለመዘከርና ከእነ ሙሉ ማንነቱ ለትውልዱ ለማስተላለፍ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ በመተባበር፣ ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ ሥራዎች ተሰርተዋል፣ ከእነዚህም መካከል ስሙን ከፍ አድርጎ የሚዘክር ሐውልት እና በስሙ የተሰየመ አደባባይ እንዲሁም በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ እና ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ባለአንድ ፎቅ ሕንጻ ናቸው፣ ሆኖም ግን በሀገራችን በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ የተነሣ የተዘጋጀውን የቅዱስ ያሬድ ሐውልት በስሙ በተሰየመው አደባባይ ላይ ማቆም አልቻልንም በዛሬው ዕለት በመካከላችን የተገኙት ብፁዕ አባታችን በሀገረ ስብከታችን በኩል የከተማ አስተዳደር ጽ/ቤቱን አነጋግረውልን ችግሩ በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት ብፁዕነታቸውን አሳስበዋል ፡፡
ወደፊትም ሀገራዊ ጥራት እና ደረጃውን የጠበቀ እና በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ሊማሩበት የሚያስችል የዜማ ትምህርት ቤት ለመሥራት በሰ/ጉ/ጽ/ቤት በኩል ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” የዛሬዋ ዕለት ከቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ በዓል ባሻገር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠባበቁ የነበሩት ነቢያትና አባቶች “ፈኑ እዴከ እም አርያም” እጅህን ከአርያም ላክ እያሉ ደጋግመው ጥሪ ከማቅረባቸውም በላይ አንደሚወለድም ጭምር በመንፈስ ተረድተው የሰበኩበት የልደት ዋዜማ ነው፣ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ አስቀድመው ነቢያት የሰበኩለትን፣ ሐዋርያት የተጋደሉለትን ጌታ ሊያገለግል የተጠራ የቅዱሱ እግዚአብሔር አገልጋይ ነው፣ ቅዱሱን ወንጌል ለማገልገል እና በቤቱ ለመመላስ በእግዚአብሔር ያልተጠራ ሰው የለም፣ የሰማ የለም እንጅ የእግዚአብሔርን የጥሪ ድምፅ ሰምተው እና እንደ ቅዱስ ያሬድ ቆርጠው የወጡት ግን በብዙ ጸጋ ተባርከዋል፣ የቤተ-ክርስቲያን አባት ለመሆንም በቅተዋል፣ ስማቸውም በትውልዱ ልብ ውስጥ ታስቦ ይኖራል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ቅዱስ ያሬድ ተስፋ የሚያስቆርጥ የሕይወት ጉዞውን ታግሶ በመቆየቱ እና በእግዚአብሔር ላይ ተስፋ በማድረጉ ዓለም የማይችለውንና ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልበትን ሰማያዊ ጥበብ ተቀብሏል፣ በዚህም ቤተ ክርስቲያን ከሰማይ እንጅ ከዓለም የተዋሰችው አንዳች ነገር እንደሌለ ተረድተናል፣ ስለሆነም ይህንን ሰማያዊ ኃብት መጠበቅ፣ ማስፋፋት፣ ከዓለማዊነትም ጋር አለመደባለቅ ያስፈልጋልና ጠብቁ ፣ አስፋፉ ፣ለትውልድ የሚሆን ነገርም ሥሩ በማለት አሳስበዋል፡፡
በደብሩ ተሰርቶ በከተማ አስተዳደሩ እንዲዘገይ የተደረገውን የቅዱስ ያሬድ አደባባይና ሐውልት አስመልክቶም በውጭው ዓለም የሀገር ባለውለታዎችን መዘከር የተለመደ ነገር ነው ፣እኛ ሀገር ግን ብዙ ይቀረናል ፣ኢትዮጵያ ሀገራችን የራሷ ዜማና የዜማ ስልት እንዲኖራት ከማድረግ ጀምሮ በዓለም የልዩነት ማማ ላይ ከፍ ላደረጋት ለቅዱስ ያሬድ ይቅርና ለበርካታ ሀገር ወዳድ ወገኖቻችንም መንገድና አደባባይ በሰማቸው ተሰይሞላቸዋል፣ የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል፣ ቅዱስ ያሬድም የሀገር ባለውለታ ነውና በደብሩ የተጀመረው በጎ ነገር እንዲፈፀም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እንነጋገራለን፣ በአጭር ጊዜም ችግሩን ፈትተን እውን እናደርገዋለን በማለት አባታዊ ቃላቸውን አረጋግጠዋል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ