የአዲስ አበባና ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ጉብኝት አደረጉ ፣ አባታዊ መመሪያም ሰጡ

ታህሳስ 9 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ወንዶሰን ገ/ሥላሴ እና የየክፍሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል ፣ አባታዊ መመሪያም ሰጥተዋል::

በመርሐ ግብሩ ላይ አጭር ንግግር ያቀረቡት የክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ወንዶሰን ገ/ሥላሴ ” በዛሬው ቀን በክፍለ ከተማችን ያለውን ጽህፈት ቤታዊ አሠራር እና አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ለማየት እና የሥራ ጉብኝት ለማድረግ እንዲሁም እና አባታዊ የሥራ መመሪያ ለመስጠት በጽህፈት ቤታችን ስለተገኙ እጅግ ደስ ብሎናል:: ክፍለከተማችን ከሀገረ ስብከቱም ሆነ ከአድባራት ገዳማቱ ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት ጤናማ ከመሆኑም ባሻገር የዕዝ ሰንሰለቱን የጠበቀ ነው ብለዋል::

ምቹ የሆነ የቢሮ አደረጃጀት እና የቢሮ ዕቃ አለመኖር፣ የሥራ ማስኬጃው እጅግ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ወቅቱን ጠብቆ አለመለቀቁ ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ክትትል ማነስ እና የመሳሰሉት ችግሮች ለክፍለ ከተማው የሥራ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆናቸውን አስረድተው ሁሉም ችግሮቻችን በብፁዕነትዎ መልካም ፈቃድና አባታዊ መመሪያ ሰጭነት እልባት እንደሚሰጣቸው አምናለሁም ብለዋል::

በመቀጠልም በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች “ከአሁን በፊት በቆየንባቸው የሥራ ጊዜያት በሀገረ ስብከቱ የበላይ የሥራ ኃላፊዎች ተጎብኝተን አናውቅም፣ ዛሬ ግን ያለንበትን ሁኔታ ለማየት እና አባታዊ የሥራ መመሪያ ለመስጠት ብፁዕነትዎ ወደ እኛ መጥተው ስለጎበኙን ደስታችን ወደር የለውም እናመሰግናለን፣ ክፍለ ከተማችን ባሉት የሥራ ዘርፎች ላይ በተሰጠን ኃላፊነት ውጤታማ የሚባሉ ሥራዎችን ሠርተናል፣ እየሠራንም እንገኛለን፣ ለዚህም ስኬት ዋና ምክንያቱ ከክፍለ ከተማችን ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ያለነው የሥራ ባልደረቦች ጤናማ ግንኙነት መኖሩ እንደሆነም ገልፀዋል::

በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” የዛሬዋ ዕለት ለዚህ ክፍለ ከተማ የተሰጠች ቀን ናት፣ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በምትመጡ ስአት የመጣችሁበትን የተቋም ሥራ በአጭር ጊዜ በማስፈጸም ትሄዳላችሁ እንጅ የግልም ሆነ የመላውን ሠራተኛ ጥያቄ የምትጠይቁበት ሁኔታዎች አልነበሩም፣ የትኛውንም ሥራ ከመጀመራችንና ከመሥራታችን በፊት መተያየት፡መተዋወቅ ይቀድማል፣ ዛሬ ደግሞ እናንተን ብቻ ሳይሆን የሥራ ቦታችሁንም ጭምር ለማየት መጥተናል፣ ክፍለ ከተማው ያሉበትን ችግሮችም ተረድተናል፣ እንዲሟሉላችሁ የምትፈልጓቸውን በቂ የሥራ በጀት እና የሥራ መሳሪያዎች ባቀረባችሁት ጥያቄዎች ውስጥ ተረድተናል፣ ጥያቄዎቹን እንደ አስፈላጊነታቸው እየመረመርን በየደረጃው እንመልሳለን በማለት አረጋግጠዋል፡፡

አያይዘውም እንደ ሁልጊዜው ሁሉ በዛሬው ዕለትም የማሳስባችሁ ነገር ቢኖር ትልቅ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን የተልእኮ ሥራ ማለትም ቅዱስ ወንጌሉን ጊዜና ትኩረት ሰጥታችሁ እንድታጠናክሩ፣ በበጀትና በጊዜ የተመጠነ የሥራ ዕቅድ አዘጋጅታችሁ በዕቅድ እንድትመሩ፣ እንዲሁም በምትሠሩት የትኛውም የሥራ እንቅስቃሴ በላይኛው የኃላፊነት እርከን ካሉት አካላት ብቻ እንዳትጠብቁ ፣ ይልቁንም የላይኛውን አካል የሚቀሰቅስና የሥራ ተነሳሽነቱን የሚጨምር ጥያቄ እንድትጠይቁ፣ ራሳችሁንም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በሚመጥን መልኩ እንድታንጹ ነው በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈው የጉብኝትና የውይይት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

ይኸው ክፍለ ከተማ በሥሩ ያሉትን አድባራትና ገዳማት በማስተባበር በደብረ ልዕልና ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን ለብፁዕነታቸው የአቀባበል መርሐ ግብር ማድረጉም የሚታወስ ነው::

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ