በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ የሚውል የግንባታ ቅድመ ጥናት መሪ እቅድ ቀረበ

ታህሳስ 06/ 2013 ዓ/ም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ተገኝተው በቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ ላይ የተሰሩ ቤቶችና የተለያዩ ህንጻዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር አካለወልድ ተሰማ፥ የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ፥ የካቴድራሉ የአስተዳደር ሠራተኞች፥ የሰበካ ጉባኤ አባላት እና ሊቃውንት እንዲሁም በርከት ያሉ ምእመናን ተገኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ በካቴድራሉ የሚገነቡ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ የሚውሉ የግንባታ ቅድመ ጥናት መሪ እቅድ ቀርቧል። ለመንፈሳዊ አገልሎት መስጫ ሊገነቡ ከታቀዱት ግንባታዎች መካከል የክርስትና ቤት፥ የአስከሬን ማረፊያ ፍትሓት መፍቻ ክፍል፥ ደጀ ሰላም፥ ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ፥ የአብነት ትምህርት ቤት፥ የሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ፥ የአስተዳደር ሠራተኞች ማረፊያ፥ የዕቃ ግምጃ ቤት፥ የካህናት ማረፊያ፥ የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ፥ የካቴድራሉ ጽህፈት ቤት፥ ዘመናዊ ሁለ ገብ አዳራሽ እና የጸበል ቤት ሲሆኑ ለማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ የሚውሉት ደግሞ ቤተ መጻሕፍትና ሕትመት ቤት፥ ሆስፒታል፥ የአቅመ ደካሞች ማረፊያ፥ የከተማ ግብርና፥ የዳቦና እንጀራ መጋገሪያ፥ ትምህርት ቤት ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ኮሌጅ እና የንግድ ህንጻዎች መሆናቸውን በቅድመ ጥናቱ መሪ እቅድ ተገልጿል።

እነዚህ የሚገነቡ ህንጻዎች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ላቅ ያለ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚኖራቸው ሲገለጽ፥ ለግንባታው አጠቃላይ ከ1.4 ቢልዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያስፈልግ በቅድመ ጥናቱ መሪ እቅድ ተብራርቷል። በእቅድ የተያዘ ግንባታም ከመጪው መስከረም 2014 እንደሚጀምር ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ መመህር አካለወልድ ተሰማ በቀረበው ቅድመ ጥናት መሪ እቅድ አስመልክተው ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ህንጻዎች ለመገንባት ማቀዳቸውን እጅግ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን በመግለጽ መሪ እቅዳቸውን ቶሎ ማጽደቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት አጣምራ የያዘች መሆኗን በማውሳት፡ ስለ ቀረበው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ግንባታ ቅድመ ጥናት መሪ እቅድ ሰበካ ጉባኤውን አመስግነዋል።

መሪ እቅዱ እጅግ የተቀደሰና ደስ የሚያሰኝ አሳብ መሆኑን በመግለጽ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውለውን ትምህርት ቤት እንዲያስቀድሙ አሳስበዋል።

አያይዘውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የካህናት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማብራራት በታቀደው እቅድ፡ ካቴድራሉ ቅድሚያ ስለ አገልጋዮች ካህናት ቢያስብ የተሻለ መሆኑን በመጠቆም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲሰምር የካህናት ሁለንተናዊ ኑሮ በሚገባ መታየት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ያቀረቡትን መሪ እቅድ መልካምና ለቤተ ክርስቲያኒቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በመግለጽ በዚሁ እንዲቀጥሉ በማበረታታት ዝግጅቱን በጸሎትና ቡራኬ ተዘግተዋል።

መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ወሲሁን ተሾመ