ለአዲስ አበባ እና ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እና ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

ታህሳስ 3 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ፕሬዘዳንት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/ብ ሩፋኤል የማነ ብርሃን እና ሠራተኞች፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል ሊቃነ መናብርት እና ጸሐፊዎች እንዲሁም የደብሩ ሰ/ት/ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በክፍለ ከተማው አስተባባሪነት በተዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁልን የአቀባበል መርሐ ግብር በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ተደርጓላቸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ አጭር የሥራ ሪፖርት ያቀረቡት የክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅ መ/ብ ሩፋኤል የማነ ብርሃን “እኛ ዛሬ ወደዚህ ቦታ የጋበዝነዎት የብፁዕነትዎን አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ለመቀበል ነው ፣ የልጅነት ጥሪያችንንም አክብረው ስለተገኙልን እናመሰግናለን፣ ባለፈው የ2012 ዓ/ም በጀተ ዓመት የነበረው የክፍለ ከተማችን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ አመርቂ የሚባል ነው፣ ሆኖም ግን ወደፊት የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች በተለይም ደግሞ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እንደሚቀረን እናምናለን፣ ከብፁዕነትዎ አባታዊ መመሪያ እየተቀበልን የቀረንን ሁሉ ሠራተኞቻችንን በማስተባበር በዕቅድ እየተመራን እናከናውናለን ብለዋል::

በክፍለ ከተማው ሥር የሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተወካይ መልአከ ገነት መ/ር መዝገቡ “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ እንዲተዳደር የተወሰነውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተከትሎ ብፁዕነትዎ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆነው ስለተመረጡ ደስ ተሰኝተናል፣ እንኳን ደህና መጡልን፣ ሀገረ ስብከታችን አሰልች የሆነ የቢሮ ክራሲ አሠራር፣ አግባባዊ ያልሆነ የገንዘብ ዝውውር/ሙስና/፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እና ሌሎችም መሰል ችግሮች እንዳሉበት እንረዳለን እነዚህ ችግሮች ይቀረፉ ዘንድ ከብፁዕነትዎ አጠገብ እንቆማለን፣ የቤተ-ክርስቲያናችንንም ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ እናፋጥናለን በማለት የአብሮነት ቃላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በመቀጠልም የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሰላምና ጸጥታ የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ደረጄ ግርማ ቤተ ክርስቲያን የሰላም መገኛ የመጽናናት ደጅ ናት፣ በውስጡ ሰላም ያጣና ማንነቱ የተረበሸ ሰው ሁሉ ሄዶ የሚረጋጋባት መሆኗንም አምናለሁ፣ የሰላም መገኛ የሆነችው ይችው ቤተ ክርስቲያን ለከተማችን አዲስ አበባ ብሎም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታ ከአሁን በፊት እና አሁን ከምታደርገው በላይ ትኩረት ሰጥታ እንድትሠራም ጥሪዬን አቀርባለሁ፣ እኛም እንደ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎችም ለሀገርና ለወገን በሚጠቅሙ መልካም ነገሮች ሁሉ አብረን ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “ሽልማቱ የተሰጠኝ የሥራ ፍሬየ ውጤት ሆኖ አይደለም፣ ምክንያቱም እኔ የመጣሁት በቅርብ ነው፣ ሆኖም ግን ይበርቱ አብረንዎት ነን ለማለትና አደራ ለመስጠት እንደሆነ ገብቶኛል፣ ስለ ስጦታችሁም አመሠግናለሁ: ዛሬ በእናንተ መካከል በመገኘቴና የክፍለ ከተማውን የሥራ እንቅስቃሴ በሪፖርት መልክ በመስማቴ ደስ ብሎኛል፣ ወደፊትም በዚሁ ጥንካሬና አንድነት ቀጥሉ በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ነን፣ በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል::

አያይዘውም አሁን በሰማነው የ2012 ዓ/ም በጀተ -ዓመት ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት ላይ የተሰበሰበው የፐርሰንት ገቢ ከፍተኛ መሆኑን እና በክፍለ ከተማው ሥር ባሉት አድባራትና ገዳማት የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ነው፣ ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያን ትልቁ የተልእኮ ሥራ ቅዱሱን ወንጌል ለጨለማው ዓለም ማወጅ እና ማስተማር ነው፣ ስለሆነም ክፍለ ከተማውም ሆነ አድባራትና ገዳማቱ በዚህ ቅዱስ አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥታችሁ እና ተግታችሁ ሥሩ፣ አእምሯችን በቅዱስ ወንጌሉ ይልማ፣ እጆቻችን ደግሞ ለበጎ ሥራ ይንቀሳቀሱ፣ የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ልማት በሰፊው ልብ እና በጥልቁ አእምሮ ላይ የሚደረግ ልማት ነው፣ ለዚህ ልማት ትፋጠኑ ዘንድ አደራ እላለሁ በማለት አሳስበዋል::

በተያያዘ ዜናም የ2012 ዓ/ም በጀተ-ዓመት የሀገረ ስብከቱን 20% ድርሻ በአግባቡና በወቅቱ የከፈሉ እና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለሠሩ አድባራትና ገዳማት በክፍለ ከተማው የተዘጋጀ የእውቅና ምስክር ወረቀት በመስጠት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል::

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ