በደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባለ 360 ፉካ መቃብር እና ደጀ ሰላም ተመረቀ
ሕዳር 27/2013 ዓ/ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት በኮ/ቀ/ክ/ከተማ ስር የሚገኝ የደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባለ 360 ፉካ መቃብር እና ደጀ ሰላም ሲመረቅ፤ 2ኛ ሁለገብ ሕንጻ መሠረተ ድንጋይ ተጥሏል።
በሕንጻ ምርቃቱም ሆነ መሠረተ ድንጋዩ ማስቀመጥ ሊቃውተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተሠራ ሕንጻ ተመርቆ አዲሰ ለሚሠራ ሁለገብ 2ኛ ሕንጻም መሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።
በዕለቱ ከደብሩ አገልጋዮች ወረብ፥ ቅኔና ግጥም የቀረበ ሲሆን የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መልአከ አርያም አምደወርቅ ደሴም ደብሩ ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት በቀዳሚነቱና በጥንታዊነቱን የሚታወቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ደብሩ ጥንታዊና ታሪካዊ በመሆኑ በነገሥታቱ እንክብካቤ ሲደረግለት የነበረ፣ ከ200 ዕድሜ በላይ ያስቆጠረ ጥንታዊ መሆኑን በማስታወስ ስሙ መልዕልተ አድባራት ቀራንዮ መድኃኔዓለም ተብሎ እንዲጠራ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጥያቄአቸውን አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም ለጥያቄአቸው አወንታዊ መልስ ሰጥተዋል። ደብሩ ያን ያህል ዕድሜ ያስቆጠረ ወላዴ ኲሉ ስለ ሆነ በጥያቄአችሁ መሠረት “መልዕልተ አድባራት ቀራንዮ መድኃኔዓለም” ተብሎ እንዲጠራ ሲሉ መልካም ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል።
በደብሩ የተሰሩ ባለ 360 ፉካ መቃብር እና አዳራሽ እንዲሁም ሌሎቹን የሚገራርሙ ሥራዎች በማያቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ። ቤተ ክርስቲያን የሥርዓት ቤት ናት። በዚህ ቤተ-ክርስቲያን የተሰራ መሠረተ ልማት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኑ መልካም ሥርዓት የሚያስቀጥል ስለሆነ አጠናክራችሁ ቀጥሉበት ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ልማት በመሥራት በገቢ ራስዋን እንድትችል ማድረጉን መልካም መሆኑን ገልጸዋል።
ብፁእነታቸው አያይዘውም ሙስና ከቤተ ክርስቲያን እናስወግደዋለን፤ ስሙም በቤታችን እንዲነሳ አንፈልግም እሱ ለዓለም እንተወዋለን ካሉ በኋላ እውቀትና መንፈሳዊነት አጣምረው የያዙ ሰዎች በየሙያቸው ተሰማርተው እንዲሰሩ በማድረግ ሁነኛ ለውጥ እናመጣለን በማለት ተስፋ ሰጪ መልእክት ተናግረዋል።
በመጨረሻም በደብሩ የተጀመረው መልካም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
መምህር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ፡- በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ