የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ እንደሚደግፉና ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ዛሬ ባወጡት መግለጫ ገለጹ
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቀርቧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጥቅምቱ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን ስም መነገድ ይቁም!
ከጥቅመኞች፣ ከሥልጣን ጥመኞች እና ከልዩ ተልእኮ አራማጆች ቤተ ክርስቲያናችንን እንጠብቃለን!
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ከጥቅምት 11 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባው በአጀንዳነት ይዞ እንዲመለከታቸው፣ ሀገር አቀፉ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ በአቀረባቸው ዐበይት ወቅታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ተወያይቶ ተፈላጊውን ውሳኔ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ለሰንበት ት/ቤቶች ግንባር ቀደም ተሳትፎ አጽንዖት በመስጠት የተላለፈው ይኸው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና መመሪያ፣ ቤተ ክርስቲያናችን እየደረሰባት ያለውን ውጫዊ ተጽዕኖ እና ጥቃት በመቋቋም እና በመከላከል ጠንክራ ለመውጣት የሚያስችላት ከመኾኑም በላይ፣ ተጋላጭ ያደረጋትን የውስጣዊ አሠራር ክፍተት በመቅረፍ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ ለመፈጸም የሚያበቃት በመኾኑ፣ የልጅነት ጥያቄአችንን ተቀብለው ተገቢውን ምላሽ ለሰጡን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችንና ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ያለንን ልባዊ ምስጋና እና አክብሮት አስቀድመን እናቀርባለን፡፡
ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጥያቄዎች መካከል አንዱ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አስተዳደራዊ ጉዳዮች የተመለከተ ነበር። በሀገረ ስብከቱ በሰው ሀብት አስተዳደር በኩል የሚታየው አድሏዊነት፣ ጎጠኝነት፣ የሥራ ዋስትና ማጣት እና እንግልት፤ በፋይናንስ አሠራር እና በንብረት አያያዝ ረገድ የተንሰራፋው የሀብት ብክነት እና ምዝበራ በመባባሱ፣ በተለዋዋጭ ጥቅመኞች በየጊዜው መወረሩ በአገልጋዮች ላይ ያስከተለው የሥነ ምግባር ዕጦት እና በምእመናን ላይ ያሳደረው የመንፈስ ዝለት ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ጠቅላላ ውድቀት ከመድረሱ በፊት መገታት ይኖርበታል፡፡
ይህ አሳፋሪ እና አሳዛኝ ኹኔታ ሊገታ የሚችለው ደግሞ፣ ቀደም ሲል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መመሪያ ሰጪነት ተዘጋጅቶ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ እንዲተገበር የተወሰነው የመዋቅር፣ አደረጃጀት እና አሠራር ለውጥ ሲተገበር ነው፡፡ የለውጥ ትግበራ ቅድመ ዝግጅቱ፣ በ2006 ዓ.ም. ተጀምሮ የነበረ ቢኾንም፣ ሕገ ወጥ ጥቅማቸውን በሚያቋርጥባቸው አማሳኞች አድማ ሒደቱ እንዲሰናከል ተደርጓል፡፡ በመኾኑም፣ የሰንበት ት/ቤት አንድነት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለውን አሠራር በማስፈን ኹለንተናዊ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችለው ጥናታዊ ለውጥ በቁርጠኝነት እንዲተገበር ምልዓተ ጉባኤውን በአጽንዖት ጠይቆ ነበር።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም፣ ጥያቄያችንን፥ “ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ስለማሻሻል” በሚል በያዘው አጀንዳ ውስጥ አካቶ እና በጥያቄያችን ላይ ተመሥርቶ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት የሚያደርገውን የሕጉን አንቀጽ 50 ንኡስ አንቀጽ(1) ድንጋጌ መርምሯል፡፡ በዚሁ ምርመራውም፣ ሀገረ ስብከቱ በአሁኑ ወቅት ካለው የሰው ኃይል ክምችት፣ የገንዘብ እና የንብረት ሀብት አንጻር፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የቅርብ አመራር እና ክትትል እንደሚያስፈልገው ታሳቢ በማድረግ፤ አበ ብዙኃን የኾኑት ቅዱስ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ርእስ እንደመኾናቸው አጠቃላይ አመራር የመስጠት ሓላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ፤ የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌው በአፈጻጸሙ፥ ለአድሏዊ አስተዳደር እና ለሀብት ምዝበራ የፈጠረውን ክፍተት ለመግታት ብሎም ለካህናት እና ለምእመናን የቆየ ምሬት እልባት ለመስጠት፣ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 50 ንኡስ አንቀጽ(1) ድንጋጌ እንዲሻሻል ወስኗል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው የድንጋጌ ማሻሻያ፣ ርእሰ መዲናዪቱ አዲስ አበባን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ያደረገው አንቀጽ፣ ወጥቶ፣ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ እንደ ሌሎቹ አህጉረ ስብከት ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ ተመድቦለት የሚመራ ይኾናል፡፡
በዚህም መሠረት ምልዓተ ጉባኤው፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ መድቧል።
የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሕግ አውጪ እና ወሳኝ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተደነገገን አንቀጽ፥ በከፊል ወይም በሙሉ የመለወጥ፣ የማሻሻል እና የመሰረዝ ሙሉ ሥልጣን ያለው በመኾኑ፣ የአህጉረ ስብከት ማዕከል የኾነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ በስብከተ ወንጌል፣ በሰው ሀብት አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝ እና በንብረት አጠባበቅ ረገድ ውጤታማ ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያስፈንና በአርያኣነት እንዲታይ፣ አስፈላጊ እና ወቅታዊ ነው ብሎ ያመንበትን የአንቀጽ 50 ድንጋጌ አሻሽሏል።
የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት፣ በመዋቅሯ ኹሉ የበላይ አካል የኾነና ልዩ ልዩ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣት እና የመወሰን ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች፥ ኦርቶዶክሳውያን ካህናት፣ ምእመናንና ወጣቶች ኹሉ የመቀበል፣ የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ግዴታ አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ልዕልና ሊጠበቅ የሚችለው፣ በበላይነት የመምራት እና የማስጠበቅ ሓላፊነት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፈው ውሳኔ ሲከበር እንደኾነ አሌ የሚባል አይደለም።
ይኹን እንጂ፣ በላይኛው መዋቅር ዙሪያ የተኮለኮሉ እና መዋቅሩን የግል መጠቀሚያ በማድረግ ጥቅማቸውን ለማስቀጠል የቋመጡ፣ በተዋረድም በመዋቅር ውስጥ የተሸሸጉ፣ በአፍቅሮተ ነዋይ የሰከሩ እና ለተንደላቀቀ ሥጋዊ ኑሯቸው በኔትወርክ ተሳስረው እየደለሉ ጥቅማቸውን ከማሳደድ በቀር ሞያ የሌላቸው አማሳኞች፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ወሳኔ ከመቀበል ይልቅ ተግባራዊነቱን በልዩ ልዩ የአድማ ቅስቀሳ ለማስተሃቀር መሰለፋቸው አያስገርምም። ለማይሞላው ቀፈታቸው እና ገደብ አልባ ፍትወታቸው ሲሉ ቤተ ክህነታችን ከብልሹ አሠራር እንዲላቀቅ አይሹም።
በባሕርይዋ ቅድስት የኾነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በአስተዳደር ድክመት የተነሣ ዘመኑን ባለመዋጀቷ እየተነቀፈች መዘበቻ ብትኾን፣ ዕድሜ ዘመናቸውን በትምህርት ያሳለፉ ሊቃውንት፣ ሌት ተቀን በአገልግሎት የሚደክሙ ካህናት እና መምህራን የሚገባቸውን መብት እና ጥቅም ተነፍገው ቢንገላቱ፣ ቀናዒ ምእመናን በእነርሱ ነውር ተሸማቅቀው በዐደባባባይ ቢያፍሩ፣ ጥቂት የማይባሉትም ተሰነካክለው ወደ ሌላ ቢኮበልሉ በአጠቃላይ፣ ቤተ ክርስቲያን ከመሠረታዊው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና ከማኅበራዊ ልማት ብትደናቀፍ አንዳችም አይገዳቸውም፡፡ በነባሩ የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ፣ ቅዱስነታቸው ዕለታዊ እና ዝርዝር ጉዳዮችን በቅርበት ከመከታተል አኳያ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው፣ ሕገ ወጥ ሀብትን ለግላቸው እያደለቡ መቀጠልን ይመርጣሉ፡፡
እነኚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ርእሰ መንበር እና ርእሰ አበው የኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ጠብቀው እና አስጠብቀው አጠቃላይ አመራር የመስጠት ሓላፊነት እንዳለባቸው በቅጡ አይረዱም፤ በአንድ ሀገረ ስብከት ሳይወሰኑ በኹሉም አህጉረ ስብከት፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ እና መመሪያ ለማስፈጸም ቅዱስነታቸው በበላይነት የሚከታተሉ እና የሚቆጣጠሩመኾኑን አያስተውሉም፡፡ እያወቁም ቢኾን፣ አዛኝ እና ተቆርቋሪ መስለው በመቅረብ፣ ቅዱስነታቸው ከሚታወቁበት መርሕ እና አባታዊ አቋም ጋራ የማይስማማ ባዕድ ዐሳብ በማንሣት ውዥንብር ሲፈጥሩ ታይተዋል። በቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት በተለይ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ፣ በአባቶች መካከል የሚንጸባረቀውን ጤናማ የሐሳብ ልዩነት እና አቋም መነሻ አድርገው የራሳቸውን ቅርፅ በመስጠት፣ የማይደግፉትን ወገን ለማሳጣት የሔዱበት ርቀት፣ የገቡበትን ፅልመታዊ እንቅስቃሴ እና ድብቅ የጥፋት አዘቅት የሚያጋልጥ ነው።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን በማሻሻል አግባብ የልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌ እንዲለወጥ ውሳኔ ካሳለፈበት ሥርወ ምክንያት እና አግባብ ውጪ ሌላ ትርጉም እየሰጡ፣ በቅንነት በጎ ሐሳብ ሲሰነዝሩ የነበሩ ብፁዓን አባቶችን ባልተገባ መንገድ እየፈረጁ ልዩነትንና ውዝግብን ለማስፋት ሞክረዋል። በዋናነትም ቅዱስነታቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተገዢ የመኾናቸውን የማይናወጥ አቋም በተሳሳተ መንገድ በመረዳት፣ በማስረዳት እና ከፋፋይ ቅስቀሳ በማካሔድ፣ ከላይ እስከ ታች የዘረጉትን የጥቅም ትስስር ለማስቀጠል፣ ቤተ ክርስቲያንን አዳክሞ ለፀራውያን ጥቃት እና ለፖሊቲከኞች ጣልቃ ገብነት አሳልፎ ለመስጠት የደረሱበትን የድፍረት ጥግ በገሃድ ለመገንዘብ ችለናል።
በሌላው ጽንፍ ደግሞ፣ በዘመኑ የጎሠኝነት ደዌ የተመቱ፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት መጠበቅ ዕንቅልፍ የሚነሳቸው፣ እንደየዘመኑ የፖለቲካ ቅኝት አሰላለፋቸውን እየለዋወጡ ቤተ ክርስቲያኒቱን መቀፍደድ የሚፈልጉ፣ የመንፈስ ቅዱስን ይኹንታ በሥጋዊ መሻታቸው ለመተካት የሚያደቡ ወደረኞች፣ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች እና የኅትመት ውጤቶች ቅዱስነታቸውን በማጥላላት፣ ባልዋሉበት እና በማያውቁት ጉዳይ በሐሰት ለመክሠሥ የሚያደርጉት አፍራሽ እንቅስቃሴ፣ ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ታሪካዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለመዳፈር የቃጡበት ነው፡፡
በመኾኑም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፦
በመዋቅር ውስጥም ኾነ በውጪ ኾናችኁ፣ ቅዱስነታቸውንና ሌሎችንም ብፁዓን አባቶችን አስመልክቶ ሐሰተኛ ንግግር የምታስተላልፉ፣ ጸያፍ እና ተገቢ ያልኾነ ጽሑፍ የምታሰራጩ፣ ገጸ ሥዕሎቻቸውንና ምስል ወድምፃቸውን በመጠቀም፣ ሐሰተኛ ዘገባ በመሥራት ስም በማጥፋት ተግባር ላይ የተሰማራችኹ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸሁ እንድትቆጠቡ፤ ይልቁንም የሚያቀራርብ፣ አንድነትን የሚያጸና እና ሰላምን የሚያስፍን በጎ ፍሬ ያለው ተግባር ላይ እንድትሰማሩ አጥብቀን እናሳስባለን።
ቅዱስ ፓትርያርኩ በፈቃደ እግዚአብሔር ለታላቋ ቤተ ክርስቲያን የተሾሙ፣ እስከ ዓረፍተ ዘመናቸው በመንበሩ የሚቆዩ የኦርቶዶክሳውያን ኹሉ አባት ናቸው። በግለሰቦች ጩኸት፣ ስሜት እና ፍላጎት ሥልጣነ ፕትርክናውንና ዘመነ ክህነታቸውን የሚሽር እና የሚለወጥ አንዳችም ነገር አይኖርም። ይህንም በማድረግ በዘመናችን ጥቁር ታሪክ እንዲመዘገብ ከቶ አንፈቅድም።
በመኾኑም፣ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላም ለማደፍረስ እኵይ ዓላማ አንግባችኹ የተሰለፋችኹ ከአጥቢያ እስከ ከፍተኛ ሓላፊነት ያላችኹ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ ስም የምትነግዱ፣ “ተገፉ፤ ጫና ተደረገባቸው” ባይ የጨለማው ቡድን አጋፋሪዎች፣ ያለፈው ዘመን ይበቃልና ከዚኽ ድርጊታችኹ ታቅባችኹ ንሥሓ እንድትገቡ እንመክራለን።
በደመ ክርስቶስ የተመሠረተች፣ በመንፈስ ቅዱስ የጸናች ቤተ ክርስቲያናችን፣ በእንዲህ ዓይነቱ የእናንተ ክፋት አልቆመችም፤ በእናንተም አትፈርስም። ይልቁንም፣ ያለፈው ዘመን ይበቃል፤ ወደ ልባችኹ ተመለሱ፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ከቅዱስነታቸው እና ከብፁዓን አባቶች ላይ እጃችኹን ሰብስቡ።
ያለው እና ተከታዩ ትውልድ የሚረከባት ቤተ ክርስቲያን፥ የጥቅመኞች፣ የጎሠኞች፣ የሥልጣን ጥመኞች እና የልዩ ተልእኮ አራማጆች መፈንጫ ስትኾን በባይተዋርነት እንደማንመለከት አስረግጠን ለመናገር እንወዳለን።
ከምእመናን ቤተሰቦቻችን ጋራ በመኾን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ ያሳለፋቸው ጥናታዊ ውሳኔዎች ሳይሸራረፉ በአፋጣኝ ተግባራዊነታቸው እንዲጀመር፣ ከቤተ ክህነታችን አመራር እና ከአስተዳደር ጎን በመቆም፣ የበኩላችንን ሞያዊ እገዛ በማበርከት እና የምልዓተ ወጣቱን ድጋፍ በማስተባበር ቤተ ክርስቲያናችንን ከምዝበራ፣ ከማንኛውም ተጽዕኖ እና ጥቃት እንታደጋለን፤ ክብሯንና ልዕልናዋን ተረክበን እናስረክባለን።
በመጨረሻም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀደም ሲል ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፥ የመንበረ ፕትርክናውን ክብር፣ መልካም ስም እና ዝና በሚመጥን የፕሮቶኮል ሠራተኞች እና የልዩ ልዩ ዘርፍ አማካሪዎች ቡድን በማዋቀር እና በማደራጀት፣ እየተስተዋሉ የሚገኙ ችግሮች እና ክፍተቶች እንዳይደገሙ ይደረግ ዘንድ በአክብሮት እያስታወስን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጎን በመቆም ለአፈጻጸሙ የሚቻለንን ጥረት እንደምናደርግ በልጅነት አንደበት ለማሳሰብ እንወዳለን።
ቸሩ እግዚአብሔር የአገራችንን ሰላም የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
ኅዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም.
ምንጭ፡- የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ