ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር ለሚገኙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ እንዲተዳዳር ቅዱስ ሲኖዶስ ስለወሰነው ውሳኔ ማብራሪያ ሰጡ

ህዳር 4 ቀን 2013ዓ.ም የጉራጌና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ስለተሻሻለው የሕገ ቤተ-ክርስቲያን ድንጋጌ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ልዩ ሀገረ ስብከት መባሉ ቀርቶ ራሱን ችሎ እንዲተዳደር የ2013ዓ.ም የወርኃ ጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የወሰነውን ውሳኔ በአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር ለሚገኙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ሀገረሰብከት የስብሰባ አዳራሽ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በስድስቱ ክፍላተ ከተሞች ሥር ለሚገኙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ማብራሪያ መሰጠቱን የዘገብን መሆኑ ይታወሳል፡፡
ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲተዳዳር ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ ገለጻ ማድረጉ ዋናው ዓላማው መደነጋገርና ግራ መጋባት እንዳይኖር፣ አገልግሎት በአግባቡ እንዲከወን፣ በአንድ ሃሳብ በጋራ ለመመራትና መከፋፈል እንዳይኖር ያግዛል በማለት ከዚህ በፊት በተደረገው ማብራሪያ ላልተገኙት በአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር ለሚገኙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ “ልዩ ሀገረ ስብከት” በመሆኑ ምክንያት የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች ያሉበት መሆኑን የተገነዘበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባኤ “ራሱን ችሎ እንዲተዳደር” ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሊቀ ጳጳስ እየተመራ ሥራውን እንዲያከናውን ውሳኔ ማስተላለፉንና በቅዱስ ሲኖዶስ የነበረውን ለሀገረ ስብከቱ የሊቀ ጳጳስ አመዳደብ ሂደትንም እንዴት እነደነበረ ብፁዕነታቸው አብራርተዋል፡፡

ከአሁን በኋላ ሀገረ ስብከቱ የሚኖረው አሠራር እንደ በፊቱ ሳይሆን ምቹ ያልሆኑ አሠራሮችን በማረም፣በሙሉ ኃላፊነት፣ሕገ ቤተክርስቲያንንና ቃለ-አዋዲን መሠረት በማድረግ፣ችግሮችን ለይቶ በማወቅና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ዘመኑን የዋጀ የአሠራር ሂደት እንደሚከተል ገልጸዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱን ችግሮች ለመለየትና ውጤታማ ሥራዎችን ለመከወን ጥናት እንደሚካሄድ፣ጥናቱም በሚመለከታቸው አካላት አስተያየት ተስጥቶበት እንደሚጸድቅና አስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ቅጥር፣ዝውውር፣እድገት እንደማይኖር መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

ሥራዎችን በእቅድ ማከናወን እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ያለ እቅድ መመራት ልጓም በሌለው ፈረስ እንደመጋለብ ይቆጠራል፣ ሀገረ ስበከቱንም ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጥ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ያለ እቅድ መመራቱ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“አገልግሎት ጥሪ በመሆኑ መንፈሳዊነት ውበቱ ነው” ስለዚህም ዘረኝነትና ሙስናን አጥብቀን በመቃወም የተሰጠንን ሐላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ያስፈልጋል በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በአስተዳደር ሂደት ደሃ የሆነውን የሀገረስብከቱን አሠራር ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለውጥና ውጤት ማምጣት የሁሉም አገልጋይ ሐላፊነት ነው ብለዋል፡፡

መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስበከቱ ዘጋቢ