የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ችግሮች ለመፍታትና ሁለንተናዊ ዕድገቱን ለማፋጠን ያለመደነቃቀፍ መስመራችንን ጠብቀን በጋራ እንሮጣለን………ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ: የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች እና ሠራተኞች:የሰባቱም ክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ በስብከተ ወንጌል በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የሥራ መመሪያ ተሰጠ፣ አጭር ውይይትም ተካሄደ ።
የሥራ መመሪያውንና የውይይት መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “በወርኃ ጥቅምት በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እንደ አንድ አጀንዳ አድርጎ በመነጋገር፣ በየጊዜው የሚፈጸሙ ብልሹ አሠራሮችንና ጉድለቶችን በሚገባ ገመገመ፣ ለዚህ ሁሉ ግድፈት የዳረገውን የሕገ ቤተ-ክርስቲያን ድንጋጌ አሻሽሎ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሱን በቻለ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ወሰነ፣ ከአሁን በፊትም ሀገረ ስብከቱን የተወሰነ ጊዜ ቆይተውበታል፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩም ችግሮቹን ያውቃሉ፣ ስለዚህ እርስዎን መድበናል ስባል የብፁዓን አባቶቼንና የቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ በማክበርና በመታዘዝ እሽ በጀ ብየ የቻልኩትን ሁሉ ከእናንተ ከልጆቼ ጋር ለማድረግና የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ወደ ትልቁ የቤተ-ክርስቲያን መጥቻለሁ ብለዋል::
በመቀጠልም ይህንን ትልቅ ሀገረ ስብከት ለመምራት በድጋሚ ዕድሉን ካገኘሁ በተሰጠን ሜዳ ላይ ያለመደነቃቀፍና ያለማንም ጣልቃ ገብነት መስመራችንን ጠብቀን በጋራ እንሮጣለን፣ ከአሁን በፊት በነበረው አሠራር በቀረቤታ፣ በዝምድ እና በጥቅም ትስስር ይሠራ እንደነበር እናውቃለን እነዚህ አሠራሮች ግን ነውር ከመሆናቸውም ባሻገር አሮጌው ባቡር የሚጓዝባቸው አሮጌ ሀዲዶች ናቸው፣ አሁን ግን አዲስ የባቡር ሀዲድ ሠርተን ረጅም ዓመት ባካበቱት የሥራ ልምዳቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው የተሻለ ደረጃ የደረሱ እና ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸውን የቤተ-ክርስቲያንን ልጆች ይዘን የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣትና በየመስመራችን በመሮጥ የሀገረ ስብከቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማሳካት እንሮጣለን ለዚህም የሀገረ ስብከቱ አሁናዊ ችግር ያገናዘበ የአሠራር ሲስተም እንዘረጋለን በማለት ገልጸዋል::
በመጨረሻም ከሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ከክፍላተ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች እና በሀገረ ስብከታችን ሥር ከሚገኙ አድባራትና ገዳማት ጋር በመተባበርና እጅ ለእጅ በመያያዝ የሀገረ ስብከቱን ደረጃ እንደሚያስጠብቁና የካህናቱን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል::
በሀገረ ስብከቱም ሆነ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ባሉት የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ለሚገኙት ሁሉም የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተመደቡበት የሥራ ቦታ በመገኘትና ተሰፎሮ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት እና መደነቃቀፍ የመሮጫ መስመራቸውን ጠብቀው እንዲሮጡና የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ለሀገረ ስብከቱ ለውጥ ብሎም ለቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲሠሩ አባታዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ