የቤተ-ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ክቡር አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ፣ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ኃላፊው መ/ር ባህሩ ተፈራ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰባቱም ክፍላተ ከተሞች የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎችና የአድባራትና ገዳማቱ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ በስብከተ ወንጌል ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን መልእክት መሠረት ያደረገ”ማደግህ በነገር ሁሉ ይገለጥ” (1ጢሞ 4:15) የሚል የመነሻ ዳሰሳዊ ሐሳብ በሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ኃላፊው መ/ር ባህሩ ተፈራ የቀረበ ሲሆን በቀረበው ዳሰሳዊ የመነሻ ሐሳብ ላይ የሰብከተ ወንጌል አገልግሎት ለቤተ-ክርስቲያን የተሰጠ ትልቅና ዘላለማዊ እንዲሁም መለኮታዊ አደራ ነው : ለዚህ ክቡርና ሕይወት ለሚድንበት አገልግሎት ደግሞ እኛ ተጠርተናል፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ስናሰፋና ስናጠናክር የተሰጠንን መንፈሳዊ አደራ ከመወጣታችን ባሻገር ሁለንተናዊ የቤተ-ክርስቲያንን ዕድገት ለማፋጠን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል::

በመቀጠልም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት፣ በየጊዜው የሚደረግ የአገልጋይነት ዝግጅት ማድረግ፣ የመልካም ሥነ-ምግባር ባለቤት መሆን: የጸሎት ሕይወትን መለማመድና ለአገልግሎቱ ያለንን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ማሳደግ ከአንድ መንፈሳዊ አገልጋይ የሚጠበቁ መንፈሳዊ ግዴታዎች ናቸውና በሚገባ ልንፈፅማቸው ይገባል ካሉ በኀላ ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ በየአድባራትና ገዳማቱ የሚደረጉ ጉባኤያትን ማጠናከር እና መገምገም በሰባክያን መካከል ወጥነት ያለው ግንዛቤ መፍጠርና የመሳሰሉትን የመፍትሔ ሐሳቦችንም አቅርበዋል::

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የስብሰባው ታዳሚዎች “ስብከተ ወንጌል የቤተ-ክርስቲያን ትልቁ ተልእኮ ሆኖ እያለ በሀገረ ስብከቱም ሆነ በአድባራትና ገዳማቱ የሥራ ኃላፊዎች ግን የሚገባውን ያክል ቦታ አልተሰጠውም፣ ዛሬ ግን በዚህ የከበረው ወንጌል ዙሪያ ስለተወያየን ደስ ተሰኝተናል፣ ወደፊትም የውይይት መድረኮች እንዲዘጋጁና ችግሮቻችንን በዚህ መልኩ እንዲፈቱ፣ ለወንጌል አገልግሎቱም የሚገባ ቦታና ክብር እንዲሰጠው እንፈልጋለን፣ እኛም የተሰጠን መንፈሳዊ አደራ በመወጣት የሕዝበ-ክርስቲያናችንን ሕይወት ለመታደግ የቻልነው ሁሉ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል::

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ መገናኘት የማንችልበት ከባዱና ፈታኙ ወቅት አለፈ፣ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተልእኮና ተግባር ስብከተ ወንጌል ነው: ይህንን ትልቅ ተልእኮ ደግሞ ጊዜ ሰጥተን ልንነጋገርበትና አብዝተን ልንሠራበት ይገባል፣ እኛ ተስፈኞች ብቻ አይደለንም ይልቁንም ዘላለማዊ ተስፋን የሚያሰንቅ ቃሉን የምንሰብክ ነን እንጅ: በችግሮቻችን ላይ ሁላችንም ብዙ ብናወራ አይጠቅመንም ነገር ግን ወደ መፍትሔው አምርተን ውጤት ላይ መድረስ አለብን፣ ለዚህም ለወንጌል አገልግሎቱ የሚመጥን ዕውቀትና ልምድ ያላችሁ መምህራን በመካከላችን ስላላችሁ ከእናንተ ጋር በመሆንና በመተባበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችንን እናሰፋለን ፣ ወጥ የሆነ አገልግሎትም እንፈጥራለን ፣ስብከተ ወንጌል ክፍሉ ከሰባክያን ጋር በየጊዜው የሚገናኝበትን ሥርዓትም እንዘረጋለን፣ ነገ ግን በእኛ የሥነ ምግባር ጉድለት የተነሣ ቅድስት ቤተ- ክርስቲያናችን እንዳትነቀፍብን የሕይወት እንቅስቃሴያችንን ከቃሉ ጋር እናስማማ በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል ። ወደፊትም እንደዚህ አይነቱ መርሐ ግብር በስፋትና በምልዓት እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል::
በመጨረሻም ከክፍላተ ከተሞች የስብከተ ወንጌል ክፍል እና ከሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ጋር በመሆን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴውን የሚያጠናክርና የሚያሰፋ ሰባት አባላት ያሉት አንድ ኮሚቴ አዋቅሮ፣ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት መርሐ ግብሩን በጸሎት አጠናቋል::

የአቋም መግለጫውን ታነቡ ዘንድተጋብዛችኀል

ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም
የአቋም መግለጫ

እኛ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት ሰባክያነ ወንጌል የሚቀጥለውን ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ እናቀርባለን፡፡

1.የቤተክርስቲያን አፈ ጉባዔ የሆነው ስብከተ ወንጌል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በየጊዜው በተለያየ ጊዜ የመከራ ውርጭ ቢመታውም በስብከተ ወንጌል ላይ ጠንክረን በመሥራት ስብከተ ወንጌሉ በሰፊው እንዲበቅል፣ እንዲያብብ እና የሚጠበቅበትን አስደናቂ ፍሬ እንዲያፈራ ጠንክረን እንሠራለን፡፡

2.እኛ ሰባክያን ዘመኑን የዋጀ እና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ዘመናዊ ስብከት፣ የረዘመውን በማሳጠር የተንዛዛውን በመጠቅለል ከሚቆጠረው ገንዘብ ይልቅ የማይቆጠሩ ነፍሳት ወደ መንጋው እና ወደ እግዚአብሔር ቤት ተሰብስበው እንዲገቡ ሌት ተቀን ያለ እረፍት እንሠራለን፡፡

3.እኛ ሰባክያን እጅ ለእጅ ተያይዘን የቤተክርስቲያንን መብት በማስከበር ከማህሌት ወደ ቢሮ፣ ከዓውደ ምህረት ወደ ጽ/ቤት የሚደረገውን የሊቃውንት ፍልሰት በፅኑ ተቃውሞ እና በትጋት ሠርተን እናስቆማለን፡፡

4.ለምናገለግለው ሕዝብ እና ምዕመን በሥነ ምግባር የበለፀጉ ሰባኪያን እና መምህራን በሚያስደንቅ ለውጥ ተወርዋሪ ብርሃናማ ከዋክብት በመሆን እናገለግላለን፡፡

5.እኛ ሰባካያን ከዘር፣ ከቡድን፣ ከሥነ ምግባር ብልሽት እና ቤተ ክርስቲያንን ከሚያሰድብ እና ከሚያስነቅፍ የትኛውም ክፉ ሥራ በመራቅ ለተጠራንበት ዓላማ በፅናት እንቆማለን፣

6.እኛ ሰባኪያን እና መምህራን ከተለመደው የስብከተ ወንጌል አሰራር በተለየ መልኩ ወጣቱን ከሱስ፣ ባለትዳሮችን ከመለያየት፣ ህፃናቱን በመልካም ሥነ ምግባር በማሳደግ እንጥራለን፣

7.ሰባኪያን የዕውቀት እጥረት ያለባቸውን ሰባክያን በሥልጠና እና በመሳሰሉት የራሳችን እና የሌሎችን አቅም ለማሳደግ እንጥራለን፡፡

ጥቅምት 2013 ዓ.ም


መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ-መ/ር ዋሲሁን ተሾመ