የጥቅምቱ የ2013 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻው ስነ ሥርዓት በጸሎት ተከፈተ
የ2013 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 11 ከቀኑ 10:00 ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡር ቆሞስ አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎተ ምኅላ ተደርጎ፣ ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ኪዳን ደርሶ በጸሎት ተከፍቷል።
በመክፈቻው መርሃ ግብር ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የስዊድን ሊቀ ጳጳስ “አኀዊነ ኢታንክርዋ ለእንተ ትመጽአክሙ መከራ ፥ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤” (1ጴጥ 4:12) በሚል የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ቃል መነሻነት አሁን በቤተ ክርስቲያን እየደረሰ ላለው መከራ ሊያስደንቀን፣ እንዲሁም ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለ ታሪክ እና ለኢትዮጵያ ምሰሶ ናትና ውለታዋን ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያን አሁን ላለው ሁኔታም ልትመክርበት ይገባል፣ እንዲሁም ወደ ቀደመችው እንድትመለስ ቅዱስ ሲኖዶስ ሊጠይቅ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የመክፈቻው መርሃ ግብሩ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በጸሎት ተዘግተዋል።
መልካም የሐዋርያት ጉባኤ ያርግልን!
መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ