39ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ በሰላም ተጠናቀቀ

ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ በዛሬው እለት ጥቅምት 05/2013 ዓ.ም ተጠናቋል ፡፡ ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሃግብር የአውስትራሊያ፣የጣሊያንና አከባቢዋ፣ የሊባኖስና የተባባሩት ኢምሬቶች አህጉረ ስብከቶች ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ከሪፖርታቸውም እንደተደመጠው የኮሮና ቫይረስ ለመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ከባድ እንቅፋት መሆኑን ገልጸው ነገር ግን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን እንዳስፋፉ፣በብሔርና በሃይማኖት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን የተለያዩ እርዳታዎችን አንዳደረጉ፣አብያተክርስቲያናትን እንዳስፋፉ፣ ሰላም በሌለበት አከባቢ ስለ ሰላም አብዝተው እንደሠሩ ጠቅሰዋል፡፡

አህጉረ ስብከቶቹም ጠንካራ ጎናቸውን በማጠንከርና በማጎልበት፤ እንዲሁም ደካማ ጎናቸውን በማስተካከልና በማረም በአዲሱ ዓመት የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ አቅደዋል፡፡
በቋሚ ሲኖዶስ መልካም ፍቃድ የተቋቋመው የሽልማት ኮሚቴ የሁሉንም አህጉረ ሰብከቶች የሥራ ፍሬ በቋሚ ሲኖዶስ በተሰጠው የመመዘኛ መስፈርት በመገምገም የሽልማት መርሃግብር አዘጋጅቶ ሽልማቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አህጉረ ስብከቶች እንዲበረከት አድርጓል፡፡

በሌላ መልኩ የጠቅላይ ቤተክህነትን መመሪያ በማክበር ማለትም እስከ ሐምሌ 30/2012ዓ.ም ቅጽና ፐርሰንት የተከፈለበትን ስሊፕ አስገቡ ብሎ ያዘዘውን መመሪያ በወቅቱና በሰዓቱ አስቀድመው የተገበሩ ሦስት አህጉረ ሰብከቶች (ከሚሴ ሀ/ስ፣ድሬደዋ ሀ/ስ እና መተከል ሀ/ስ) ልዩ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡

ተጠሪነቱ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሆነው ታላቁና አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የልዩ ልዩ ተሸላሚ ተብሎ በመሰየም ምስጋና ተችሮታል፡፡

በነበረው መርሃግብር ለሁሉም አህጉረ ስብከቶች የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈው፣በጸሎትና በቡራኬ የ2013 ዓ.ም 39ኛውአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ በሰላም ተጠናቋል ፡፡

በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

ፎቶ፦ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ የሀገረ ስብከቱ ፍቶግራፈር