የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች እጅግ የተሳካ አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተገለጸ !!!
በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ መሠረት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2012 ዓመተ ምህረት በመንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች ላይ እጅግ የተሳካ አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተገለፀ።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ህይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ በ39ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ አለምአቀፍ ጉባኤ የሀገረ ስብከቱን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ በሥሩ የሚያስተዳድራቸው 246 ገዳማትና አድባራት የሚገኙ መሆኑን ገልፀው በበጀት ዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ ገዳማትና አድባራት መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከአደጋ ዝግጁነት ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግና በሽታውን ለመከላከል የተተገበሩ እንቅስቃሴዎች አመርቂ እንደነበሩ ተገልጿል።
የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን በተመለከተ የተሰሩ ዐበይት ተግባራት በዚሁ ሪፖርት የተካተቱ ሲሆን በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤ ያላሰለሰ ጥረት በዘጠኝ ክፍላተ ከተማ የሚገኙ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች በጠቅላላው 391,750 ካ.ሜ በሀገረ ስብከቱ ስም የይዞታ ማረጋገጫ (ካርታ) ማግኘት መቻሉ ተጠቁሟል።
ከ60 በላይ የሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ መደረጉ ፣ የተራቆቱ አብያተ ክርስቲያናትን በደን ለመሸፈን ፕሮጀክት ተቀርጾ ከ42,500 በላይ ችግኞች እንዲተከሉ መደረጉ ፣ የ 3 አዳዲስ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ምስረታ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ በሕግ አግባብ አብያተ ክርስቲያናቱ ተባርከው አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉ በሪፖርቱ ከቀረቡ በርካታ ነጥቦች ጥቂቶቹ ናቸው።
በቃለ ዓዋዲው ደንብ መሠረት ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ፈሰስ ከሚያደርገው 65 % በተጨማሪ 2,478,644.44 /ሁለት ሚልየን አራት መቶ ሰባ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ አርባ አራት ብር ከአርባ አራት ሳንቲም/ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድርጅቶች ፣ ኮሌጆችና ገዳማት የበጀት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በተጨማሪም በማኅበራዊ ዘርፉ ለአኅጉረ ስብከት ፣ ለአብነት ት/ቤቶች፣ ለነዳያንና ለችግረኞች 13,129,334.02 / አስራ ሦስት ሚልየን አንድ መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አራት ብር ከ ዜሮ ሁለት / ብር ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ኅብረት ያለውን አለኝታነት ማሳየቱ ተገልጿል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ህይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ እንደገለፁት ሀገረ ስብከቱ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሰበሰበው ከመቶ 20 ፐርሰንት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከሀገረ ስብከቱ የሚጠበቀውን 65 % ብር 212,695,743.92 /ሁለት መቶ አስራ ሁለት ሚልየን ስድስት መቶ ዘጠና አምስት ሺህ ሰባት መቶ አርባ ሦስት ብር ከዘጠና ሁለት ሳንቲም/ ሙሉ በሙሉ ገቢ ማድረጉን ገልፀዋል። ይህም ካለፈው 2011 ዓ.ም ገቢ ጋር ሲነፃፀር በ2012 ዓ.ም ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ፈሰስ የተደረገው ፐርሰንት የብር 93,714,307.95 / ዘጠና ሦስት ሚልየን ሰባት መቶ አስራ አራት ሺህ ሦስት መቶ ሰባት ብር ከዘጠና አምስት ሳንቲም/ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል።
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ከእነዚህም ተግባራት ባሻገር እቅበተ እምነት ፣ ፀረ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ላይ እና አስተዳደሩን በማዘመን ሂደት ላይ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል።
በተለምዶ 22/24 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ለመትከል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ምዕመናንን ከፀጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው ማለፉ ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱ ፣ የሥራ ፈላጊ ካህናት መበራከት የሀገረ ስብከቱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የገለፁት ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በዚህ እና መሠል ችግሮች ውስጥ ቢሆንም ግን በቅዱስነታቸው አባታዊ መመሪያ ጸሎት እና በእግዚአብሄር ቸርነትና ቅዱስ ፈቃድ ያስመዘገባቸው ተግባራት በርካታ መሆናቸውን ሪፖርቱ አክሏል።
ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ ከሰበሰበው ፐርሰንት ላይ በአብላጫ የሰበሰበውን ከ200 ሚልየን ብር በላይ እየተካሄደ በሚገኘው መደበኛ ጉባኤ ላይ በክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ ፤ አማካይነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ተረክበዋል።
የ39ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ አለምአቀፍ ጉባኤ አባላት ክቡር መልአከ ህይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በሳል አመራር እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በበጀት ዓመቱ ላስመዘገቡት የላቀ አስተዋፅኦ በደማቅ ሁኔታ ምስጋና አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ከምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ ነዉ።
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ይጎብኙ
ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
ተሌግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese