የቀድሞ አባቶቻችን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ አርዓያ ሊሆን እንደሚገባ የመ/ፓ/ጠ/ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ አሳሰቡ
ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ/ም ከስዓት በኋላ በነበረው የሁለተኛው ቀን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ውሎ ከመጀመሪያው ቀን የቀጠሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አህጉረ ስብከቶች ዓመታዊ የሥራ ሪፓርት በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊው መጋቤ ሐዲስ ሐዋዝ ተጫነ በንባብ ቀርቧል::
ከስዓት በኋላ ከቀረቡ ዓመታዊ የሥራ ሪፖርቶች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የኪራይ ቤቶችና ሕንጻዎች ድርጅት አንዱ ሲሆን የብዙዎችን ቀልብ በሚስብ መልኩ በዶክመንተሪ ፊልም አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴውንና ሪፖርቱን አስደምጧል::
በዳሰሳ ዶክመንተሪው እንደቀረበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የየዘመኑ መሪዎች እና ተከታይ ምዕመናኗ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪክ የማይዘነጋው የትውልድ አሻራ ከመሆኑም ባሻገር ለዛሬይቱ ቤተ-ክርስቲያን ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆኑም ተገልጿል::
ከነገሥታቱ ዘመን ጀምሮ ፍቅር ቤተ ክርስቲያን ባላቸው የሀገር መሪዎች፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች በውርስና በስጦታ የተገኙ እንዲሁም ደግሞ ቤተ-ክርስቲያኒቱ በራሷ ገንዘብ የሠራቻቸው እና በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ጽርሐ ምኒልክ ሕንጻ፣ አስቦት ሕንጻ ፣ ዘውዲቱ ሕንጻ፣ መንትያዎቹ (አቡነ ቴዎፍሎስ) ሕንጻ እና ሌሎችም በርካታ ስያሜ ያላቸው ብዙ ቤቶች እንዳሉም በሪፓርቱ ላይ የቀረበ ሲሆን እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች ግን በደርግ መንግሥት የተወረሱና በሂደት በተደረገው ከፍተኛ ድርድርና ስምምነት ብዙዎችን ማስመለስ እንደተቻለ፣ የቀሩትንም ለማስመለስ በሂደት ላይ መሆኑንም አሳውቋል። በዚህ ንብረት የማስመለስ ሥራ ላይ በእጅጉ ለደከሙ ስዎችም የቤተ ክርስቲያን ማኅደሮች በማለት ምሥጋና አቅርቧል::
ከመንግሥት ጋር በተደረገ ድርድር ከተመለሱ እና በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ወጭ ታንጸው ወደ ሥራ ከገቡ ቤቶችና ሕንጻዎች ኪራይ ዘጠና ሁለት (92) ሚሊዮን ብር መገኘቱንም አሳውቋል::
በመጨረሻም የቤቶችና ሕንጻዎች ድርጅት ሪፓርትን አስመልክቶ አጭር ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መ/ፓ/ጠ/ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ቅድስት ቤተ-ክርስቲያናችን የዛሬ አርባ (40) ዓመት አካባቢ ባለ አሥራ ሁለት ፎቅ ሕንጻ በመገንባት እና በሥነ-ሕንጻ ዘርፍ ያላትን ዕውቀት በማሳየት ከመንግሥትም ቀዳሚ ነበረች፤ ይህ መልካም ጅምር ዛሬ እኛ ለምንመራት ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ የቀድሞ አባቶቻችን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ እና ተሻጋሪ ራዕይ ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ምሳሌ እና ወኔ በመሆኑ እኛም የእነሡን ፈለግ ተከትለን ያልተመለሱትን የቤተ-ክርስቲያን ንብረቶች እንዲመለሱ በማድረግ፣ ሌላ የገቢ አማራጭና ምንጭ የሚሆኑ የልማት ሥራዎችን በመስራት የቤተ ክርስቲያናችንን ልማታዊ እንቅስቃሴ በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ በአሠራር የተደራጀች፣ በፋይናንስ የተጠናከረች ቤተ ክርስቲያን ማስረከብ ይገባናል በማለት ጉባኤውን አሳስበዋል::
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ