የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክያን ትውልድ በማነፅ የምታደርገውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ/ም ብፁዓን ወቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ :ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት: የጠ/ቤ/ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽና የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣የሁሉም የአህጉረ ስብከቶች ሥራ አስኪያጆችና ተወካዮች ፣ በቤተክርስቲያኒቱ ሥር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የሁለተኛውን ቀን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል::
በቅዱስ ፓትርያሪኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልካም ፈቃድ እና ጋባዥነት የጉባኤ መክፈቻ ትምህርተ ወንጌል የስዊድንና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ በሆኑት አረጋዊ አባት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ተሰጥቷል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንቶ ለሀገራችን ኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ሆና ከማገልገሏም ባሻገር ለመላው ዓለም ጭምር የዕውቀትና የሥነ ምግባር ፋና ወጊ ሆና የኖረች መንፈሳዊ ተቋም ናት::
ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ወንጌሉን በማስተማርና በማጥመቅ፣ እጓለ ማውታ የሆኑ ሕጻናትን አሳድጋ ለቁም ነገር በማብቃት፣ ጧሪ አልባ አረጋውያንን በመንከባከብ፣ ትውልዱን በሥነ-ምግባር እና በሃይማኖት በማነፅ ለሀገር ያበረከተችው አስተዋፅኦ በቃላት የሚገለፅ ባይሆንም አሁን እየተፈጸመባት ያለው ግፍ ግን ውለታዋን የተዘጋ አስመስሎታል:: በአንዳንድ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳውያን በመሆናቸው ብቻ በአስቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ለዘመናት የደከሙበት ሀብት እና ንብረታቸው ወድሟል፣ ከሞት የተረፉትም ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል:: ይህ ሁሉ ግን እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ብላ ለሀገር ለምትጸልይ ቤተ-ክርስቲያን አይገባትም ነበር ብለዋል::
በመቀጠልም በዚህ ሰላሳ ዘጠንኛ(39ኛ) የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የቤተ-ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ችግር በመፈተሽ እና በመወያየት የቤተ ክርስቲያናችን ጉድለት ምንድነው? መነሻውስ የቱ ጋ ነው ? እንዴትስ እንፍታው በማለት በሚገባ እንድንወያይበት እፈልጋለሁ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የተመሠረተችበትን ዋና ዓላማ ቅዱስ ወንጌሉን አጠናክራ እንድታስተምር፣ ከተለያዩ የገንዘብ ምንጮች የምታገኘውን የገንዘብና የንብረት ገቢ በሚገባ እንድትሰበስብ፣ የገንዘብ አስተዳደሯን እንድታዘምናንና እንድታጠናክር እንዲሁም ደግሞ ተከታይ ምዕመናኗን በምትችለው አቅሟ ሁሉ እንድትረዳ፣ ከሁሉ በላይ ግን ክርስቲያናዊ የሥነ-ምግባር ትምህርትና አስፍታና አምልታ ለትውልዱ በማስተማር አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውን የሥነ-ምግባር ውድቀት በማሻሻል ወላጆቹንና አሳዳጊዎቹን የሚያከብር ፣ ሀገሩን የሚወድ እና ለሃይማኖቱ የቀና ዜጋ ለማፍራት ጠንክረን እንሥራ በማለት አባታዊ ጥሪ አስተላልፈው ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ሀገራዊ ችግር ለመፍታት በዚህ ዘርፍ ላይ ያላትን አቅም በሙሉ ተጠቅማ ትሠራለች ሲሉም አረጋግጠዋል::
በመጨረሻም ይህ ሰላሳ ዘጠንኛው(39ኛ) የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ወንድማዊ ፍቅር የምናዳብርበት፣ ስለራሳችን፣ ስለ ሀገር እና ስለ-ሕዝባችን እንዲሁም ደግሞ ስለ ዓለማችን ተግተን የምንጸልይበት፣ በችግሮቻችን ዙሪያ ተወያይተን ለወደፊት የመፍትሔ አቅጣጫ የምናስቀምጥበት እንዲሆን እግዚአብሔር አምላካችን ያግዘን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ::
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ጥቅምት 3/2013 ዓ/ም ተጀምሮ አሁንም እንደቀጠለ ነው::
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

ፎቶ:- ከEOTC Facebook page የተወሰደ::