የጀሞ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅ/ዮሐንስ እና ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተ-ክርስቲያን ተመረቀ
መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ/ም የአዊ እና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ : የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ-ክህነት ጽ/ቤት ሰራተኞች: በርካታ ካህናትና ሊቃውንት እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝበ ክርስቲያንና የአካባቢው ምዕመናን በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል::
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙትና ሕንጻ ቤተ-ክርስቲያኑን የባረኩት ብፁዕ አቡነ ቶማስ “ነቀዝ በማያበላሸው ሌቦችም ሰርቀው በማይወስዱት መልኩ ገንዘባችሁን በዚህ ስላስቀመጣችሁ ደስ ይበላችሁ: የሰራችሁት ሕንጻ :እግዚአብሔርና ሕዝቡ የሚገናኝበት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚሰዋበት: ቅዱሱን ወንጌል የምትማሩበት ቅዱስ ስፍራ ነው: እናንተ ጥበበኞች ናችሁ ምክንያቱም ገንዘባችሁን: ዕውቀታችሁንና ጉልበታችሁን ለእግዚአብሔር ክብር አውላችኀል በማለት ካስተማሩ በኀላ በሰራችሁት ቤት ተሰብስባችሁ ወንጌል ተማሩ: ሥጋና ደሙንም ተቀበሉ በማለትም አሳስበዋል::
በመቀጠል ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ ባደረጉት አጭር ንግግር ” ይህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶ የተጠናቀቀው እጅግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው: ይህም በደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት መ/ር ብርሃነ መስቀል ጠንካራ አመራር እና የማህበረ ካህናቱ ቀና ትብብር እንዲሁም ደግሞ የአካባቢው ምዕመናን ጠንካራ ፍላጎትና ታዛዥነት የሚያመላክት በመሆኑ ልትመሰገኑ ይገባችኀል:: ቦታው አሁንም የሚቀሩት በርካታ ሥራዎች አሉ እነዚህን ሥራዎች ለማጠናቀቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስፈላጊው ትብብር ያደርጋል ብለዋል።
በቦታው የአብነት ትምህርት ቤት ሊቋቋም እና የመማር ማስተማሩ ሂደት በአግባቡ ሊጠናከር እንደሚገባ አጽንዖት ተሰጥተው ተናግረዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት መ/ር ብርሃነ መስቀል ይህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በስምንት ወራት ውስጥ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ደስታየ ወደር የለውም : ስሜቴንም ለመግለጽ እቸገራለሁ : ከጅማሬ እስከፍጻሜ በጉልበታችሁና በሙያችሁ እንዲሁም ደግሞ በገንዘባችሁ አብራችሁን በመሰለፍ ለዚህ እንዲበቃ ያደረጋችሁ በሙሉ ምስጋና ይድረሳችሁ በማለት አመስግነዋል::
ጥር 8/1996 ዓ/ም በጥቂት ካህናት እና የአካባቢው ምዕመናን ትብብር ተመስርቶ ለአሥራ ስድስት ዓመታት ያክል ያገለገለው ቤተ ክርስቲያን እጅግ ጠባብ ስለነበር በከፍተኛ መነሳሳት ጥር 4/2012 ዓ/ም የተጀመረው አዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በስምንት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለምርቃት መብቃት እፁብ ድንቅ የሚያሰኝና የደብሩን አስተዳደር ሠራተኞችና የአገልጋይ ካህናት ጥንካሬ እንዲሁም የአካባቢው ምዕመናን ከፍተኛ ትብብር የሚስገነዝብ ከመሆኑም ባሻገር ረጅም ዓመታት ፈጅተው በመታነፅ ላይ ላሉ እና ፍጻሜ ላላገኙ ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናትም ትልቅ ግንዛቤ እንደሚፈጥር በዕለቱ የተገኙ የበዓሉ ታዳሚዎች ገልጸዋል::
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ