የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 9ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ሼይክ ሱልጣን አማን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ፣ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጲያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ፣ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ፣ አቶ ዣንጥራር አባይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ፣ ኮሚሽነር አዱኛ ደበሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላምና የሰጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ የቤተ እምነቶች አባቶችና የአዲስ አበባ መስተዳድር የመንግስት ባለ ሥልጣናት በተገኙበት በዛሬው እለት በቀን 26/2013 ዓ.ም መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል አካሄዷል፡፡
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሥሩ ሰባት የሃይማት አባላትን ያቀፈ ሲሆን ከሃይማኖት አስተምህሮ ጎን ለጎን ስለ ሀገር ሰላም የራሱን ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ከመድረኩ ተላልፏል፡፡

የዛሬው የጉባኤው መሠረታዊ ጉዳዮች የተዘረዘሩ ሲሆን እነሱም የሰላም እሴት ግንባታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከፍተኛ አመራሮችን የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ማድረግ፣ ኮሮናን መከላከል እና መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን ማካሄድ አንደሆነ ተነግሯል፡፡
በጉባኤው ላይ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልእክታቸውም “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ኤፌ 4፡3) የሚለውን የሐዋርያውን የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት በመጥቀስ ስለ ሰላም ምንነት፣ጥቅምና ውጤት፣ እንዲሁም ስለ አንድነት ጥቅም በጉባኤው ለተገኙት ታዳሚዎች ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሃይማኖታዊ ና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣና በቅንጅት እየሠራ ነው፤ ለዚህም ማሳያው ያለፈው ዓመት የመጀመሪያው የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የሰላምና የአንድነት ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በሰላም የተገመደው አንድነታችን በችግሮቻችንም ጊዜ ጎልቶ ታይቷል፣ አሁንም ሊቀጥል ይገባል፣ ኢትዮጵያዊ ሞራል ያለው ዜጋ አብዝተን ልናፈራ ይገባል ብለዋል፡፡

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልእክት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ይገኛል፣ ሰላምን ማእከል ያደረገ ሥራ እየሠራ ነው፣ አሁን ካለበት ደረጃ አድጎ የከተማውን ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ተከታታይ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ተቋሙ ኮቪድን በተመለከተ ከተለያዩ አካላት ጋር ቀጥታ በሆነ መንገድ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ሰላም ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታና ኃላፊነት ነው፣ ላፍታ እንኳን የሚዘነጋ ጉዳይ እንዳልሆነ ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ሰላም አብሮነታችንን ዘላቂ በሆነ መልኩ የሚያስቀጥልና የሰዎችን አስተሳሰብ አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንድንቀርጽ የሚያግዘን ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም በዚህ በያዝነው ዓመት የሚከናወነው 6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል፡፡
አቶ ዣንጥራር አባይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ባደረጉት ንግግር የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለፈው ዓመት ኮቪድን ከመከላከል አንጻር ላደረገው አስተዋጽኦ፣የፖለቲካ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ላደረገው ትብብር፣ ከመንግሥት ጋር በመሆንና በመተባበር ታላላቅ በዓላቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው ትብብር ምሥጋና አቅርበው ወደፊትም ከዚህ የበለጠ እንደሚሠራ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዲ/ን ሄኖክ ሀይሌ “ሃይማኖት ና ሰላም” በሚል ርእስ ተነስተው የክርስትና እምነት ስለ ሰላም አብዝቶ እንደሚነጋርና ክርስትና በራሱ ሰላም ነው መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ የአስልምና ሃይማኖት ከሰላም ጋር ያለውን ግንኙነት በመጥቀስ የሰላም አየር ማስፈን አለብን፣ ብዙ የሚያቀራርቡን የጋራ ጉዳዮች እያሉን መለያየት የለብንም፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤውም አብዝቶ ስለ ሰላም መሥራት አለበት ብለዋል፡፡
መጋቢ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን የ2012 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም እቅድ ሪፖርትንና የ2013 ዓ.ም እቅድን በጉባኤው ላይ አቅርበዋል፡፡
በመልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ በሼይክ ሱልጣን አማን እና በመጋቢ ታምራት አበጋዝ አወያይነት የ2013 ዓ.ም እቅድ ከመድረኩ አስተያየት ተሰጥቶበት ጸድቋል፡፡

በመጨረሻም የእውቅና መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን ለወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ መስዳድር ከንቲባ፣ ለአቶ ዣንጥራር አባይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ፣ ለመለሰ አለሙ፣ ለኮሚሽነር አዱኛ ደበሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላምና የሰጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ በጎ ተግባር ላከናወኑ ሚዲያዎች እና ለሌሎችም የመንግስት ኃላፊዎች የሽልማት መርሃግብር ተካሂዶ በሰላም ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ የሀገረስብከቱ ፎቶግራፈር