ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ድንገተኛ ጉብኝት አደረጉ
❖ ለክፍላተ ከተማ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች ወቅታዊ እና ጥናታዊ ድጋፎች እንደሚደረጉላቸው አስታወቁ፤
❖ በቃጠሎ ለተጎዳችው የጃቲ መካነ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን መመሪያ ሰጡ፤
❖ የሰበካዋን ምእመናን ልጆች በትሩፋት ለሚያስተምሩ የአብነት መምህር ሽልማት አበረከቱ፤
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ድንገተኛ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ጽ/ቤቱን በአፋጣኝ እና በሒደት ለማጠናከር የሚያግዙ ልዩ ልዩ ድጋፎች እንደሚደረጉ ገለጹ፡፡
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ዛሬ ዓርብ፣ መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ፣ በክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ በድንገት ተገኝተው ባደረጉት የሥራ ጉብኝት፣ ከሓላፊዎች እና ሠራተኞች ጋራ በስፋት ተወያይተዋል፡፡ የቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የቢሮ ጥበት እና የሥራ መሣሪያዎች አቅርቦት ውስንነት፣ በውይይቱ ወቅት በቀዳሚነት ከተነሡት ችግሮች ውስጥ ይገኙበታል፡፡
በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉት ሰባት የክፍላተ ከተማ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች፣ በኪራይ ቢሮዎች እንደሚገለገሉ እና ጥበቱም የጋራ እንደኾነ የጠቀሱት ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ችግሩን ከመሠረቱ ለመቅረፍ የሚያስችል ዝግጅት በማዕከል እየተደረገ እንዳለና በጥናት ምላሽ እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡ የቢሮ ዕቃዎችንና የጽሕፈት መሣሪያዎችን ጨምሮ የሥራ መሣሪያዎች አቅርቦት ውስንነትን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ የሚያስፈልገው ዝርዝር በጽ/ቤቱ ተጠንቶ ለሚመለከተው የሀገረ ስብከቱ አካል ሲቀርብ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ በዚሁ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የምትገኘውንና ባለፈው መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለኩሶ ሳይጠፋ በተረሳ ሻማ ሳቢያ የቃጠሎ አደጋ በደረሰባት የጃቲ መካነ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው፣ በቀጣይ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ለደብሩ አስተዳደር ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተጠቀሰው ዕለት ሌሊት ከተዘነጋው የሻማ መብራት የተነሣው የእሳት ቃጠሎ፣ በመቅደሱ መስተዋቶች እና በሕንፃው የተወሰነ አካል ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ይህንም በጉብኝታቸው የተመለከቱት ክቡር ዋና አስኪያጁ፣ በመብራት እና በኃይል አጠቃቀም ዙሪያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ የደብሩ አስተዳደርም በአግባቡ እንዲከታተል ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በዚሁ ደብር የሰበካዋን ምእመናን ልጆች ሰብስበው የቃል ትምህርት(ንባብ እና ዜማ) የሚያስተምሩትን መምህር ይትባረክን አግኝተው፣ በትሩፋት ስለሚያሳዩት በጎ ተግባር፣ በደብሩ የአስተዳደር ሓላፊዎች እና በምእመናን ፊት አመስግነዋቸዋል፡፡
እንደ መምህር ይትባረክ ሁሉ በሌሎችም የሀገረ ስብከቱ አድባራት፣ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ወሳኝ የኾነውንና ትውልዱን በሥነ ምግባር ለማነፅ የሚያበቃውን የአብነት ትምህርት በርእሰ መዲናይቱ ለማስፋፋት የሚተጉ የአብነት መምህራን እንዳሉ የጠቀሱት ክቡር ዋና አስኪያጁ፣ ተጠናክሮ ቢቀጥል ከከተማው ምእመናን ልጆች ተተኪ ካህናትንና ሊቃውንትን ለማፍራት እንደሚያስችል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
መምህር ይትባረክ በትሩፋት የዘረጉትን ትውልድ ተኪ ጉባኤ እንዲቀጥሉበት ለማበረታታትም፣ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ በግላቸው የካባ ሽልማት እንደሚያበረክቱላቸው አስተውቀዋል፤ የደብሩ አስተዳደር እና ምእመናንም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው መመሪያ በመስጠት፣ የዕለቱን ድንገተኛ የሥራ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ወቅታዊ እና በጥናት ላይ የተመሠረቱ ድጋፎች እንደሚደረጉ ለሓላፊዎች ገለጹ፡፡