የ2013 ዓ.ም የደመራ በዓለ መስቀል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

በዓሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የኢትዮጵያ ፕረዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡር መ/ሕይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪየጅ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ክፍል ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ታዳሚዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና በኮሮና ምክንያት ከተለመደው ለየት ባለ መልኩ እስከ 5,000 የሚሆኑ የበዓሉ አክባሪዎች በተገኙበት በድምቀትና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፦ መስቀል ቀድሞ የከፍተኛ ቅጣት መቅጫ የነበረ ቢሆንም አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ የመዳናችን ምክንያት በመሆን የሰላም ምልክት ነውና መስቀልን ስናከብር ሁላችን ለሰላም መቆም አለብን ብለዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መስቀል አዳነን ስንል ክርስቶስ አዳነን ማለታችን ነው፣ ከመስቀሉ ይልቅ ሌላ ትምክህት የለንም፣ ትምክህታችን መስቀሉ ነው። ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ አድኖናል ሰላምም ሰጥቶናል እኛም ይህንን የተሰጠን ሰላም መጠበቅ አለብን ብለዋል።

በአዲሱ ዘመን ሁሉም ነገር መስተካከል አለበት፣ ሁላችን ለሰላም ዘብ መቆም አለብን ፣ በመንግሥት በኩልም ከፖለቲካ ኃይሎች በመወያየት ችግሮችን መቅረፍ አለባቸው ሲሉ ተማጽነዋል።
በመጨረሻም አዲሱ ዘመን የሰላም፥ የፍቅርና የዕርቅ አንዲሆን በመመኘት መልእክታቸውን በጸሎትና በቡራኬ ዘግተዋል።

እኛም መስቀሉ ይቅርታና ዕርቅ የተፈጸመበት፣ ሰላም ያገኘንበት ነውና ለሰላም የበኩላችን እንወጣ እያልን እግዚአብሔር 2013 ዓ/ም የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የአንድነት እንዲያደርግልን እንመኛለን ።
መልካም በዓለ መስቀል!
መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ

photo file